የትራምፕን ጥሪ የተቀበሉ 75 ሺህ የሚጠጉ ሰራተኞች ስራ መልቀቃቸው ተሰማ
የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ስራቸውን በፈቃዳቸው ለሚለቁ የፌደራል ሰራተኞች የስምንት ወራት ደመወዝ ለመክፈል ቃል መግባታቸው ይታወሳል
![](https://cdn.al-ain.com/images/2025/2/13/273-122353-75000-us-federal-workers-accept-trump-buyout_700x400.jpg)
አንዳንድ ተቋማትም እስከ 70 በመቶ ሰራተኞቻቸውን ለመቀነስ እንዲዘጋጁ ታዘዋል ተብሏል
በአሜሪካ 75 ሺህ የሚጠጉ የፈደራል መንግስቱ ሰራተኞች ስራቸውን መልቀቃቸው ተገለጸ።
የትራምፕ አስተዳደር ከ2 ሚሊየን በላይ የፌደራል ሰራተኞች ውስጥ ቢያንስ 10 በመቶው ከስራ እንዲለቅ በማድረግ ወጪን ለመቀነስ አቅዷል።
ከስራቸው በፈቃዳቸው ለሚለቁ ሰራተኞችም ያለስራ የስምንት ወር ደመወዝ እንዲከፈላቸው እና ሌሎች ጥቅማጥቅሞችን እንዲያገኙ እንደሚደረግ መናገራቸው ይታወሳል።
የአሜሪካ የሰው ሃይል አስተዳደር ቢሮ ቃል አቀባይን ጠቅሶ ሬውተርስ እንዳስነበበው እስካሁን 75 ሺህ የፌደራል ሰራተኞች ለቀረበላቸው የስራ ልቀቁ ጥያቄ አዎንታዊ ምላሽ ሰጥተዋል።
የአዳዲስ ሰራተኞች ቅጥር ቆሞ በርካታ የመንግስት ተቋማትም የሰራተኞቻቸውን ቁጥር በመቀነስ ላይ መሆናቸውን ተናግረዋል።
አንዳንድ ተቋማት እስከ 70 በመቶ ሰራተኞቻቸውን ለመቀነስ እንዲዘጋጁ መታዘዛቸውም ነው የተገለጸው።
የሰራተኞች ማህበራት ግን "ትራምፕ የገቡትን ቃል የማይፈጽሙና የማይታመኑ ናቸው" በሚል አባላቶቻቸው ስራቸውን እንዳይለቁ ጥሪ በማቅረብ ላይ ናቸው።
የፌደራል መስሪያ ቤቶችን እና ሰራተኞችን ቁጥር መቀነስ እንደሚፈልጉ በተደጋጋሚ የገለጹት ፕሬዝዳንት ትራምፕ፥ ስራውን የሚያቀላጥፍ አዲስ መስሪያ ቤት አቋቁመው ኤለን መስክ እና ቪቬክ ራማስዋማይን ሾመዋል።
መስክና ባልደረባቸው በአሜሪካ የአለማቀፍ የተራድኦ ድርጅት (ዩኤስኤአይዲ) የጀመሩት ስራ ከ1 ትሪሊየን ዶላር በላይ ወጪን ለመቀነስ እንደሚያስችል ታምኖበታል።
የትራምፕ አስተዳደር በጥር ወር መጨረሻ የፌደራል ሰራተኞች እስከ የካቲት 6 2025 ድረስ በፈቃዳቸው ስራቸውን እንዲለቁ የኢሜል መልዕክት መላኩ ይታወሳል።
የሰራተኞች ማህበራት ያቀረቡት ክስ በፍርድቤት ውድቅ እስከሚደረግ ድረስ ቀነ ገደቡ ተራዝሞ በትናንትናው እለት በይፋ መጠናነቀቁን የዋይትሃውስ ቃል አቀባይ ካሮሊን ሌቪት ተናግረዋል።
ቃል አቀባዩዋ ውሳኔው "የአሜሪካን ህዝብ በ10 ሚሊየን ዶላሮች የሚቆጠር ሃብት ያድናል" ቢሉም ዴሞክራቶችና የሰራተኞች ማህበራት በፌደራል ተቋማት ከፍተኛ የባለሙያዎች እጥረት ይፈጥራል ሲሉ ተቃውመውታል።
የፖስታ ቤት ሰራተኞች፣ የአሜሪካ ጦር አባላት፣ የስደተኞች ጉዳይ አመራሮች እና የተወሰኑ የብሄራዊ ደህንነት ሰራተኞች ከሚሰናበቱት ውስጥ አልተካተቱም ተብሏል።