ከ9 ሺህ በላይ የዩኤስኤአይዲ ሰራተኞች ሊባረሩ እንደሚችሉ ተነገረ
ከድርጅቱ ከ10 ሺህ በላይ ሰራተኞች ውስጥ ስራቸውን የሚቀጥሉት 294ቱ ብቻ ናቸው ተብሏል
![](https://cdn.al-ain.com/images/2025/2/07/273-120426-03dc-usaid-explainer-lvgc-articlelarge_700x400.jpg)
ኢትዮጵያን ጨምሮ በአፍሪካ የድርጅቱ ሰራተኞች ቁጥር 12 ብቻ እንደሚሆንም ለእቅዱ ቅርበት ያላቸው ሰዎች ተናግረዋል
የፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ አስተዳደር ከ9 ሺህ በላይ የአሜሪካ አለማቀፍ የልማት ተራድኦ ድርጅት (ዩኤስኤአይዲ) ሰራተኞችን ለማሰናበት ማቀዱ ተሰማ።
ለእቅዱ ቅርበት ያላቸው አራት ምንጮች ነገሩኝ ብሎ ሬውተርስ እንዳስነበበው ድርጅቱ በመላው አለም ካሉት ከ10 ሺህ በላይ ሰራተኞች በስራ ገበታቸው የሚቀጥሉት 294ቱ ብቻ ናቸው።
ከድርጅቱ የአፍሪካ ቢሮዎች ውስጥ በስራቸው የሚቀጥሉት ስምንት ብቻ ናቸው፤ በእስያ ደግሞ ስምንት ይቀራሉ ብለዋል ምንጮቹ።
ዩኤስኤአይዲን ለስድስት አመታት የመሩት ብሪያን አትወድ እቅዱን "አስደንጋጭ" ያሉት ሲሆን፥ ከ9 ሺህ 700 በላይ ሰራተኞችን ማባረር የድርጅቱን ህልውና እንደሚገድል ተናግረዋል።
እቅዱ በመላው አለም በ10 ሚሊየን የሚቆጠሩ ድጋፍ ጠባቂዎችን ህይወት አደጋ ላይ እንደሚጥልም ነው ያነሱት።
ዩኤስኤአይዲን እንደገና እንዲያደራጅ ሀላፊነት የተሰጠው የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በሰራተኞች ቅነሳ እቅዱ ዙሪያ ማረጋገጫ አልሰጠም።
ትራምፕ እና የአለማችን ቁጥር አንድ ቢሊየነሩ ኤለን መስክ ድርጅቱን የአሜሪካውያን ታክስ ከፋዮችን ገንዘብ እያባከነ ነው፤ ሰራተኞቹም "ወንጀለኞች" ናቸው በማለት ይከሳሉ።
ድርጅቱ እንደአዲስ እስኪደራጅ ድረስም ቋሚ ቅጥረኞች ስራ እንዳይገቡ አዘዋል። የተወሰኑ ሰራተኞችም ከስራ መሰናበታቸውን የሚጠቁም ደብዳቤ እየደረሳቸው መሆኑን የሬውተርስ ምንጮች ተናግረዋል።
የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ማርኮ ሩቢዮ ተላላፊ በሽታዎችን ለመግታትና ረሃብን ለመቆጣጠር የተሰማሩ የድርጅቱ ሰራተኞች ስራቸውን የሚቀጥሉበትን መንገድ እየፈለግን ነው ከማለት ውጭ ስለሰራተኞች መባረር መጀመር ያሉት ነገር የለም።
የአለማችን ቀዳሚዋ የእርዳታ ለጋሽ ሀገር አሜሪካ በ2023 ለተለያዩ ሀገራት የ68 ቢሊየን ዶላር ድጋፍ ማድረጓን የሀገሪቱ መንግስት መረጃ ያሳያል።
ከዚህ ውስጥ 44 ቢሊየን ዶላሩ በአሜሪካ አለማቀፍ የልማት ተራድኦ ድርጅት (ዩኤስኤአይዲ) በኩል የቀረበ ነው።
የተራድኦ ድርጅቱ በ2023 ለ130 ሀገራት ድጋፍ ያደረገ ሲሆን አብዛኞቹ በግጭት ውስጥ የነበሩ ናቸው። ዩክሬን ቀዳሚዋ ከድርጅቱ ከፍተኛ ድጋፍ ያገኘች ሀገር ስትሆን ኢትዮጵያ፣ ዮርዳኖስ፣ ዲአርኮንጎ እና ሶማሊያ ይከተላሉ።
የትራምፕ አስተዳደር በተራድኦ ድርጅቱ ላይ ያሳለፈው ውሳኔ ከላይ በተጠቀሱት ሀገራት ድጋፍ የሚሹ ሚሊየን ሰዎችን ይጎዳል።
በድርጅቱና ድጋፍ በሚያደርግላቸው ተቋማት ውስጥ የሚሰሩ ሰራተኞችና ቤተሰቦቻቸውን ችግር ላይ እንደሚጥል ተገልጿል።