ተመድ ሰራተኞቹ በመታሰራቸው ምክንያት በተወሰኑ የየመን አካባቢዎች እርዳታ ማቆሙን አስታወቀ
ተመድ በአሁኑ ወቅት 24 ሰራተኞቹ በሀውቲዎች ታስረው እንደሚገኙ ገልጿል
![](https://cdn.al-ain.com/images/2025/2/11/243-154307-img-20250211-144127-905_700x400.jpg)
ሀውቲዎች ስልጣን ከተቆጣጠሩበት ከ2014 እና ከ2015 መጀመሪያ ጀምሮ ዋና ከተማዋን ሰንአን ጨምሮ አብዛኛውን የየመን ክፍል ተቆጣጥረው ይገኛሉ
ተመድ ሰራተኞቹ በመታሰራቸው ምክንያት በተወሰኑ የየመን አካባቢዎች እርዳታ ማቆሙን አስታወቀ።
የተባበሩት መንግስታት ድርጅት (ተመድ) ተጨማሪ ስምንት ሰራተኞቹ በሀውቲ አማጺያን በመያዛቸው በየመኗ ሰአዳ ግዛት ያለውን እርዳታ ማቋረጡን የተመድ ምክትል ቃል አቀባይ ፋርሃን ሀቅ መናገራቸውን ሮይተርስ ዘግቧል።
"ይህ ልዩና ጊዜያዊ እርምጃ የተወሰደው የተመድ ሰራተኞችና አጋሮች ደህንነታቸው ተጠብቆ እርዳታ የሚያደርሱበት ሁኔታ እንዲፈጠር ለማድረግ ነው" ብለዋል ሀቅ።
ሀቅ የእርዳታ ሰራተኞች ጥረትን ዘላቂ ለማድረግ የደህንነት ዋስትና አስፈላጊ መሆኑን ጠቅሰዋል። እርዳታ በመቋረጡ ምክንያት ምን ያህል ሰው ተጎጅ እንደሚሆን ሀቅ ግልጽ አላደረጉም።
"እርዳታው የቆመው አከባቢውን የሚያስተዳድሩት ባለስልጣናትና ተመድ በዘፈቀደ የታሰሩ የተመድ ሰራተኞች የሚለቀቁበትን ለማመቻቸትና ወሳኝ የሰብአዊ እርዳታ ለማድረስ የሚያስችሉ ሁኔታዎች መሟላታቸውን ለማረጋገጥ ነው" ብለዋል ሀቅ። ሀቅ ተመድ የሰብአዊ እርዳታ የሚፈልጉ ሚሊዮን የመናዊያንን ለመርዳት ቁርጠኛ መሆኑን ገልጸዋል።
በኢራን የሚደገፉት ሀውቲዎች ስልጣን ከተቆጣጠሩበት ከ2014 እና ከ2015 መጀመሪያ ጀምሮ ዋና ከተማዋን ሰንአን ጨምሮ አብዛኛውን የየመን ክፍል ተቆጣጥረው ይገኛሉ። ታጣቂዎቹ ከ2021 ወዲህ በደርዘን የሚቆጠሩ የተመድ ሰራተኞችን አስረዋል። በአሁኑ ወቅት በሀውቲዎች ታስረው የሚገኙ የተመድ ሰራተኞች ቁጥር 24 ነው።