እስራኤል በአንድ ቀን ውስጥ በፈጸመችው የአየር ጥቃት 79 ሰዎች ተገደሉ
በሊባኖስ የሄዝቦላህ ታጣቂዎች ይገኙበታን በተባለ አካባቢ ከፍተኛ የአየር ጥቃት መፈጸሙ ተስምቷል
በጋዛ የተመድ ከፍተኛ የሰብአዊ ጉዳዮች ሀላፊ በሰሜናዊ ጋዛ አለምአቀፋዊ ህጎች ያለከልካይ እየተጣሱ ነው ብለዋል
እስራኤል በትላንትናው እለት በፈጸመችው የአየር ጥቃት በጋዛ እና ሊባኖስ በአጠቃላይ ከ79 ሰዎች በላይ መገደላቸው ተነገረ፡፡
በጋዛ የሰብአዊ ቀጠና በሚል በታወጁ 11 ካፍቴሪያዎች የደረሰው ጥቃት የ46 ሰዎችን ህይወት መቅጠፉን ኤፒ ዘግቧል፡፡
በተመሳሳይ በደቡባዊ ሊባኖስ የመኖርያ መንደሮች ላይ የአካባቢው ነዋሪዎች አካባቢውን ለቀው እንዲወጡ ማስጠንቀቂያ በተነገረ በ11 ሰአታት ውስጥ በተፈጸመው ጥቃት 33 ሰዎች መሞታቸውን የአካባቢው የጤና ተቋማት ይፋ አድርገዋል፡፡
የእስራኤል ጦር ምንም አይነት ማስረጃ ባለቀረበበት መግለጫ የሄዝቦላህ መሠረተ ልማቶችን፣ የማዘዣ ማዕከላትን እና የጦር መሳሪያ ማምረቻ ቦታዎችን ኢላማ አድርጌያለሁ ብሏል።
በሌላ በኩል በምስራቅ ቤሩት በመኖርያ ህንጻ ላይ በተፈጸመ ሌላ የአየር ጥቃት ስድስት ሰዎች ሲሞቱ ሶስቱ ህጻናት መሆናቸውን የገለጸው የሊባኖስ ጤና ሚንስቴር በጥቃቱ 12 ተጨማሪ ሰዎች ከፍተኛ ጉዳት ደርሶባቸዋል ብሏል፡፡
የሰሞኑ የአየር ጥቃት የደረሰው አሜሪካ ተጨማሪ ሰብአዊ እርዳታ ወደ ጋዛ እንዲገባ ያስቀመጠችው ቀነ ገደብ መጠናቀቁን ተከትሎ ለእስራኤል የምታደርገውን ወታደራዊ ድጋፍ እንደማይቀንስ ባሳወቀችበት ጊዜ ነው፡፡
ምንም እንኳን አሜሪካ እስራኤል ለጋዛ ሰርጥ የሚቀርበውን የሰብአዊ ድጋፍ እንድታሻሻል ይህ የማይሆን ከሆነ የጦር መሳርያ ድጋፏን እንደምታቋረጥ ማሳውቋን ተከትሎ መጠነኛ የድጋፍ ስርጭት መሻሻሎች ቢኖሩም አሁንም በቂ አለመሆኑ ነው የሚነገረው፡፡
በፈራረሰችው ጋዛ ውስጥ ከአካባቢያቸው ተፈናቅለው በተለያዩ የመጠለያ ጣብያዎች እና ሆስፒታሎች ውስጥ የሚገኙ ፍልስጤማውያን በከፍተኛ የመድሀኒት እና የምግብ እጥረት ህወታቸው እያለፈ እንደሚገኝ ተዘግቧል፡፡
ካሳለፍነው ጥቅምት ጀምሮ ሀማስ ድጋሚ ራሱን እያደረጀበት ነው በተባለው ሰሜናዊ ጋዛ የተጠናከረውን ውግያ ተከትሎ በአካባቢው የምግብ እና መሰረታዊ እርዳታ ከደረሰ አንድ ወር ማለፉ ተገልጿል፡፡
እስራኤል ጥቃቶቹን ከመፈጸሟ በፊት ንጹሀን ከአካባቢው ለቀው እንዲወጡ ማስጠንቀቂያዎችን እንደምታስነግር ብትገልጽም በሰሜናዊ ጋዛ አሁንም 70 ሺህ የሚጠጉ ሰዎች በመጠለያዎች ውስጥ ይገኛሉ፡፡
ጋዛ የተመድ ከፍተኛ የሰብአዊ ጉዳዮች ባለሙያ በትላንትናው እለት ለጸጥታው ምክር ቤት ባቀረቡት ሪፖርት በቤተሀኑን እና ሌሎችም ሰሜናዊ ጋዛ አካባቢዎች አለም አቀፍ ህጎች ያለምንም ገደብ እየተጣሱ ነው ብለዋል፡፡