ሄዝቦላህ እና ሀማስ በእስራኤል ላይ አዲስ ጥቃት የመክፈት አቅማቸው በእጅጉ መቀነሱን አሜሪካ አስታወቀች
የአሜሪካ የብሔራዊ ጸረ ሽብር ማዕከል ሁለቱ ቡድኖች ቢዳከሙም ጦርነቱን ለረጅም ጊዜ ተቋቁመው መቀጠል ይችላሉ ብሏል
የእስራኤል ጦር 14 ሺህ የሀማስ እና 2550 የሄዝቦላ ተዋጊዎችን መግደሉን አስታውቋል
ሄዝቦላህ እና ሀማስ በእስራኤል ላይ አዲስ ጥቃት የመክፈት አቅማቸው በእጅጉ መቀነሱን አሜሪካ አስታወቀች።
እስራኤል በሊባኖስ እና ጋዛ ባካሄደችው ወታደራዊ ዘመቻ እና የአየር ጥቃት ሀማስ እና ሄዝቦላህ በሀገሪቱ ላይ ዳግም ጥቃት የማድረስ አቅማቸውን እንደቀነሰው አሜሪካ ገልጻለች፡፡
የሀገሪቱ የብሔራዊ ጸረሽብር ማዕከል ዳይሬክተር ብሬት ሆልምግሪን እንደተናገሩት ቴልአቪቭ የደህንነት ተቋማቶቿን እና የመከላከያ ሀይሏን በማቀናጀት ባለፈው አንድ አመት በሀማስ እና ሄዝቦላህ ላይ የፈጸመችው ዘመቻ በርካታ ለውጦችን የሚያስከትል ነው፡፡
ከፍተኛ ወታደራዊ እና ፖለቲካዊ አመራሮችን ጨምሮ በቡድኖቹ ተፋላሚዎች ላይ የደረሰው ኪሳራ እስራኤል ለስኬታማነት የቀረበ ዘመቻን አከናውናለች ለማለት የሚያስደፍር ነው ሲሉ ገልጸዋል፡፡
ሆኖም ሁለቱ ቡድኖች በሚንቀሳቀሱባቸው ስፍራዎች እና በቀጠናው ባሉ አጋሮቻቸው ዘንድ የሚያገኙት ድጋፍ ከፍተኛ መሆን ፈጽሞ ስጋት ሊሆኑ የማይሆኑበት ደረጃ ላይ ደርሰዋል ብሎ ለመፈረጅ ፈታኝ እንደሚያደርገው ነው ያመለከቱት፡፡
ከግጭቱ በፊት ሄዝቦላህ በምድር ዋሻዎች ውስጥ ያከማቻቸው ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ሚሳይሎች ፣ ሮኬቶችን እና የተለያዩ ተተኳሾ በእስራኤል የአየር ጥቃቶች ከፍተኛ ጉዳት እየደረሰባቸው ይገኛል፡፡
የእስራኤል መከላከያ ሃይል በዚህ ወር መጀመሪያ ላይ የሄዝቦላህ የመካከለኛ እና የአጭር ርቀት ሮኬቶች መካከል 80 በመቶ ያህሉ መውደማቸውን ማስታወቁ ይታወሳል፡፡
ምንም እንኳን እስራኤል በሄዝቦላህ የሎጂስቲክ እና የትጥቅ አቅም እንዲሁም በአመራሮቹ ላይ ሊታይ የሚችል ውድመት ብታደርስም የቡድኑ የምድር ጦር አሁንም ጠንካራ አቋም ላይ እንደሚገኝ ዳይሬክተሩ ተናግረዋል፡፡
ከዚህ ባለፈ ቴልአቪቭ ከሊባኖስ ተሻግራ የቡድኑ ዋነኛ አጋር የሆኑ ሀገራት እና ቡድኖችን ድጋፍ ማቋረጥ ላይ ያደረገችው ነገር የለም ሲል የአሜሪካ ድምጽ ዘግቧል፡፡
የአሜሪካ የብሔራዊ ጸረሽብር ማዕከል ዳይሬክተር ብሬት ሆልምግሪን ሀማስን በተመለከተ በሰጡት ማብራርያ ሀማስ ወታደራዊ አቅሙ እጅግ ተመናምኖ አጥቅቶ መሸሸግ ላይ ብቻ ትኩረቱን ያደረገ ውግያን የሚከተል የጥቂት ወታደሮች ስብስብ ሆኗል ነው ያሉት፡፡
ቡድኑ ምንም እንኳን በተጠናከረው የእስራኤል ጥቃት የተማረሩ በርካታ ወጣቶችን እየመለመለ ቢገኝም ጦርነቱ የሚቆም ከሆነ ሀማስ ወደ ቀደመ ይዞታው እና አቅሙ ለመመለስ አመታት ሊፈጁበት ይችላሉ ብለዋል፡፡
ከጥቅምት ሰባቱ ጥቃት በፊት የአሜሪካ የደህንነት ተቋማት ባወጡት መረጃ ሀማስ ከ20 ሺህ- 25 ሺህ ተዋጊዎች እንዳሉት ገምተዋል። አንዳንድ የሰላም እና ደህንነት ምርምር ተቋማት ደግሞ የቡድኑ ታጣቂዎች 30 ሺህ እና ከዛ በላይ እንደሚሆኑ ይገልጻሉ፡፡
በሀገር መከላከያ ሰራዊት ቁመና ልክ እንደተዋቀረ የሚነገርለት ሄዝቦላህ በበኩሉ ከ40 ሺህ የሚልቁ ታጣቂዎች አሉት ተብሏል፡፡
የአሜሪካ የብሔራዊ ጸረሽብር ማዕከል ዳይሬክተር በአንድ አመቱ ጦርነት በሁለቱ ቡድኖች ምን ያህል ተዋጊዎች እንደሞቱ ባይገልጹም እስራኤል 14 ሺህ የሀማስ ፣ 2550 የሄዝቦላህ ታጣቂዎችን ገድያለሁ ትላለች፡፡.