ባይደን እና ትራምፕ በስልጣን ሽግግር ጉዳይ ለመነጋገር በኋይት ሀውስ ሊገናኙ ነው
የትራምፕ ቡድን የስልጣን ሽግግሩን ለመጀመር የፈረማቸው ሰነዶች ባይኖሩም፣ ፕሬዝደንት ባይደን ሰላማዊ የስልጣን ሸግግርን ለማሳየት በኋይት ሀውስ ለንግግር ጋብዘዋቸዋል
ተሰናባቹ ፕሬዝደንት ትራምፕ ከሩሲያ ጋር እየተዋጋች ያለችውን ዩክሬንን እንዲደግፏት ሊያሳስባቸው ይችላሉ ተብሏል
ባይደን እና ትራምፕ በስልጣን ሽግግር ጉዳይ ለመነጋገር በኋይት ሀውስ ሊገናኙ ነው።
የዲሞክራቷን ፕሬዝደንታዊ እጩ ካማላ ሀሪስ ሸንፈት ተከትሎ ባይደን እና ትራምፕ በስልጣን ሽግግር ጉዳይ ለመነጋገር በኋይት ሀውስ ሊገናኙ ነው።
የትራምፕ ቡድን የስልጣን ሽግግሩን ለመጀመር የፈረማቸው ሰነዶች ባይኖሩም፣ ፕሬዝደንት ባይደን ሰላማዊ የስልጣን ሸግግርን ለማሳየት በኋይት ሀውስ ለንግግር ጋብዘዋቸዋል።
ከዲሞክራት የ2024 ፕሬዝደንታዊ እጩነት ራሳቸው ከማግለላቸው እና ምክትል ፕሬዝደንት ሀሪስ እንዲወዳደሩ ድጋፍ ከመስጠታቸው በፊት ከትራምፕ ጋር ሲወዳደሩ የነበሩት ፕሬዝደንት ባይደን የቀድሞውን እና የወደፊቱን የአሜሪካ ፕሬዝደንት ዶናልድ ትራምፕን በኦቫል ቢሯቸው ይቀበሏቸዋል። ይህ ተሰናባች ፕሬዝደንት የሚያደርጉት የተለመደ አሰራር ቢሆንም ባይደን በ2020 ባሸነፉበት ወቅት ግን ትራምፕ ይህን አላደረጉላቸውም ነበር።
"ባይደን በልምዶች፣ በተቋሞቻችን እና በሰላማዊ የስልጣን ሽግግር ያምናል" ሲሉ የኃይት ሀውስ ቃሌ አቀባይ ካሪን ጂን ፒሬ ባይደን ለትራምፕ እያደረጉትን ግብዣ በተመለከተ በትናንትናው እለት ተናግረዋል።"ያ ነው አሰራሩ። ያ ነው መሆን ያለበት።"
ባይደን እና ትራምፕ ለአመታት አንደኛቸው ሌላኛቸውን ሲተቹ የቆዩ ሲሆን በሚከተሏቸው ፖሊሲዎች ላይም ሰፊ ልዩነት ያንጸባርቃሉ። የ78 አመቱ ባይደን ትራምፕ የዲሞክራሲ ስጋት አድርገው የሚያይዋቸው ሲሆን የ78ቱ አመቱ ትራምፕ ደግሞ በባይደን ላይ አቅም የላቸው የሚል ትችት ያቀርቡባቸዋል።
ትራምፕ በ2020 ምርጫ የተሸነፉት ድምጽ ተሰርቀው እንደሆነ ያምናሉ።
ትራምፕ በዋሽንግተን በሚያደርጉት ጉብኝት ከባይደን ጋር ከመገናኘታቸው በፊት ከሪፐብሊካን ህግ አውጭዎች እና ከተወካዮች ምክርቤት አፈጉባኤ ማይክ ጆንሰን ጋር ይገኛሉ ተብሎ ይጠበቃል።
ምንምእንኳን ባይደን ሰላማዊ የስልጣን ሽግግር መኖሩን ማሳየት ቢፈልጉም በተፈለገው ልክ አልሄደም። ኃይትሀውስ እንደገለጸው ከሆነ የትራምፕ ቡድን የአዲሱን ፕሬዝደንት ካቢኔ አባላት እየመረጡ ቢሆንም ቢሮ እና የመንግስት መሳሪያዎችን ለመረከብ እንዲሁም የመንግስት ባለስልጣናትን፣ አገልግሎቶችን እና መረጃ ለማግኘት የሚያስችል ፊርማ እስካሁን አልፈረሙም።
ትራምፕ እና ባይደን የውጭ ጉዳይን ጨምሮ በበርካታ ጉዳዮች ላይ ሊመክሩ እንደሚችሉ ይጠበቃል። ተሰናባቹ ፕሬዝደንት ትራምፕ ከሩሲያ ጋር እየተዋጋች ያለችውን ዩክሬንን እንዲደግፏት ሊያሳስባቸው ይችላሉ ተብሏል። አሜሪካ ለኪቭ የምታደርገው ድጋፍ ጦርነቱን አስቆመዋለሁ ያሉት ትራምፕ ማሸነፋቸውን ተከትሎ ጥያቄ ውስጥ ገብቷል።