በጣና ሃይቅ እስከ 13 የሚደርሱ ሰዎች ያሳፈረች ጀልባ ተሰወረች
ተጓዥቹ ሐምሌ 9 ቀን 2013 ዓም ለሊት ድንች ጭነው ጉዞ መጀመራቸውን ቤተሰቦቻቸው አስታውቀዋል
ከዚህ በኋላ ሰዎችን በህይወት የማግኘት እድሉ ጠባብ መሆኑን ፖሊስ ገልጿል
በማዕከላዊ ጎንደር ዞን ምስራቅ ደንቢያ ወረዳ 13 የሚደርሱ ሰዎችን አሳፍራ በጣና ሃይቅ በጉዞ ላይ የነበረች አነስተኛ ጀልባ መሰወሯን ፖሊስ አስታወቀ።
የወረዳው ፖሊስ ጽህፈት ቤት ሃላፊ ምክትል ኮማንደር ቸርነት አስማረ፤ ጀልባዋ የተሰወረችው በወረዳው አዲሰጌ ድንጌ ተብሎ ከሚጠራ ቀበሌ አባን ላይ ጎጥ መነሻቸውን በማድረግ ወደ ጎርጎራ ወደብ ጉዞ ከጀመረች በኋላ መሆኑን ኢዜአ ዘግቧል።
ተጓዥቹ ሐምሌ 9 ቀን 2013 ዓም ለሊት ድንች ጭነው ጉዞ መጀመራቸውን ከቤተሰቦቻቸው መረጃው ለፖሊስ መድረሱን ገልፀዋል።
ተሳፋሪዎቹ ከ10 እስከ 13 እንደሚደርሱና አብዛኞቹም በስም ዝርዝር መለየታቸውን የገለፁት ምክትል ኮማንደሩ ተሳፋሪዎቹ ከመዳረሻው ጎርጎራ ወደብ እንዳልደረሱ መረጋገጡን ተናግረዋል።
ከትናንት እኩለ ቀን ጀምሮ በሁለት ቡድን የተዋቀረ የፖሊስና የባለሙያዎች ቡድን ፍለጋ እያካሄደ መሆኑን አመልክተው እስካሁን ምንም አይነት ፍንጭ ማግኘት እንዳልተቻለ አስታውቀዋል።
በዛሬው እለትም ፍለጋው መቀጠሉን ጠቁመው ተጓዦቹ ክረምት ከመሆኑ ጋር ተያይዞ ወይ በማዕበል ተወስደዋል፤ አለበለዚያም ከአቅም በላይ በሆነ ጭነት ጀልባዋ ሰምጣለች የሚል ድምዳሜ ላይ መደረሱን አብራርተዋል።
ተጓዦቹ የተነሱበት ሰዓት ለሊት ከመሆኑ ጋር ተያይዞ ፍለጋውን አስቸጋሪ እንዳደረገው ጠቅሰው ከዚህ በኋላ ሰዎችን በህይወት የማግኘት እድሉ ጠባብ እንደሆነም አመልክተዋል።
ከመነሻው መዳረሻው ያለው የውሀ ላይ ጉዞ የ15 ኪሎ ሜትር ርቀት እንዳለው አመልክትው በፍለጋው የሚገኘውን ዝርዝር ውጤት በቀጣይ ህዝቡ እንዲያውቀው እንደሚደረግ ምክትል ኮማንደር ቸርነት አስታውቀዋል።