ክብደት ለመቀነስ የምናደርገው ጥረት የማይሳካባቸው 8 ምክንያቶች
ለ18 አመታት በስነምግብ ሙያ የተሰማራችው አንጌላ ቦርጌስ ከልምዷ በመነሳት ነው ሊታረሙ የሚገባቸውን ስህተቶች የጠቆመችው
ክብደት ለመቀነስ አመጋገብን ማስተካከል ብቻ በቂ አይደለም፤ ምግብ መቀነስም በተቃራኒው ውፍረትን ሊያስከትል ይችላል ትላለች
በአለማችን ከ13 በመቶ በላይ ታዳጊዎች ጤናማ ያልሆነ የሰውነት ክብደት እንዳላቸው መረጃዎች ያመላክታሉ።
በቅርቡ የተደረጉ ጥናቶችም ከአምስት ህጻናት አንዱ ለከፍተኛ ውፍረት የተዳረገ መሆኑን ያሳያሉ።
በዚሁ ችግር ምክንያት በየአመቱ ከ2 ነጥብ 8 ሚሊየን በላይ ወጣቶች ህይወታቸው እንደሚያልፍም የአለም ጤና ድርጅት ይፋ አድርጓል።
ጤናማ ያልሆነ ውፍረት ወጥቶችን ለስኳር፣ ልብ እና ለተለያዩ የካንሰር በሽታዎች እያጋለጠ መሆኑም የችግሩን አሳሳቢነት በጉልህ ያሳያል።
ለ18 አመታት ውፍረትን ለመቀነስ የሚያስችሉ የስነምግብ ምክሮችን የምትለግሰው አሜሪካዊት አንጌላ በርጌንስ፥ ከራሷ ተሞክሮ ተነስታ ውፍረትን ለመቀነስ በሚደረግ ጥረት ውስጥ የሚታዩ ስህተቶችን አጋርታለች።
“ክብደቴን በአጭር ጊዜ ውስጥ ለመቀነስ ፈልጌ ባለሙያዎችን ሳማክር ይመክሩኝ የነበረው አመጋገቤን እንዳስተካክልና ስፖርት እንድሰራ ነበር” የምትለው በርጌንስ፥ በሂደት ያስተዋልኩትና የደረስኩበት ግን ይህ ምክር የራሱ አዎንታዊም አሉታዊ ነገር ያለው መሆኑን ነው ትላለች።
ቀጣዮቹን ስምንት ምክንያቶችም ወደኋላ የሚጎትቱን ናቸውና ልናስወግዳቸው ይገባል የሚል ምክሯን ትለግሳች።
1. "ጤናማ ምግብ እየበሉ ነው፤ ግን ለክብደት መቀነስ ጉዞዎ ጤናማ አይደለም"
ለጤና ተስማሚ የሆኑ ምግቦችን ማዛወተር እና ውፍረትን ለመቀነስ የሚረዱ ምግቦችን መምረጥ ሁለት የተቀራረቡ ግን የተለያዩ ጉዳዮች ናቸው ትላለች አንጌላ በርጌንስ።
ጤናማም ሆነው የካሎሪ መጠናቸው ከፍ ያለ ምግቦችን ስንመገብ በልኩ ይሁንም ትላለች የሰነ ምግብ ባለሙያዋ።
2. በጥቂቱ መመገብ
ክብደትን ለመቀነስ ከወትሮው በጣም ያነሰ መመገብም ተቃራኒውን ሊያመጣ እንደሚችል አንጌላ በርጌንስ ትጠቅሳለች።
“በጣም አነስተኛ ምግብ መመገብ የሰውነታችንን ምግብ የመፍጨት አቅም ስለሚቀንሰው ክብደት የመቀነሳችን ጉዞም አዝጋሚ ይሆናል” የሚል ሃሳቧን በመጥቀስ።
“ውፍረትን ለመቀነስ በሚል ቁርስ ብንዘል ወይንም ብንቀንስና ምሳ ስአት ላይ ረሃባችን ለማካካስ ከልክ በላይ ከተመገብንም ውጤቱ ያው ነው”ም ትላለች።
3. በቂ እንቅልፍ አለማግኘት
በቀን ውስጥ ከ7 እስከ 9 ስአት አለመተኛት ለሰውነታችን ክብደት መጨመር ወይም ተስተካክሎ መቀጠል ድርሻ ባላቸው ሁለት ሆርሞኖች ላይ ተጽዕኖ ያሳድራል።
ግሄሪን የተባለውን የረሃብ ሆርሞን እንዲጨምር እና ሌፕቲን የተሰኘውን በደማችን ውስጥ የሚገኝ ሆርሞን ዝቅ በማድረግ ክብደት እንዲጨምር ያደርጋል ነው የምትለው የሰነምግብ ባለሙያዋ።
“ሲደክማችሁ የረሃብ ስሜታችሁ ይጨምራና አብዝታችሁ የመብላት እድላችሁ ከፍ ይላል፤ በአንጻሩ በቂ እረፍት ስታደርጉ ሰውነታችሁ የመስከንና የደስታ ስሜት ስለሚሰማው የረሃብ ስሜን ይቀንሳል” የሚል ሃሳቧንም አጋርታለች።
4. ክብደት ይቀንሳሉ የተባሉ ምግቦችን ማዘውተር
ከባለሙያ ትዕዛዝ ውጪ የካሎሪ መጠናቸው ከፍ ያሉ ምግቦችን ወይም ፈሳሽ ነገሮችን አዘውትሮ መውሰድም ባለንበት እንድንጓዝ ያደርጋል ነው የምትለው አንጌላ በርጌንስ።
በመሆኑም በተለይ የስኳር ይዘታቸው ከፍ ያሉ ምግቦችን መቀነስ ተገቢ መሆኑንና ጤናማ ስለሆኑ ብቻ በብዛትና በተደጋጋሚ መውሰድ ውፍረት የመቀነስ ትግልን ስኬት የራቀው ያደርገዋል ባይ ናት።
5. በአጭር ጊዜ ለውጥ ካላየን በሚል ተስፋ መቁረጥ
ውፍረትን የመቀነስ ሂደት እንደ ማራቶን እንጂ የመቶ ሜትር ሩጫ አይደለም የምትለው የስነምግብ ባለሙያዋ፥ ሂደቱ ውጣውረድ ያለውና ረጅም ጊዜ የሚወስድ መሆኑን መዘንጋት እንደማይገባ ታሳስባለች።
6. ጭንቀት ማብዛት
እንደ እንቅልፍ ማጣት ሁሉ ጭንቅ ማብዛትም በውፍረት የመቀነስ ሂደት ውስጥ ትልቕ ተጽዕኖ አለው።
ጭንቀት የኮርቲሶል ሆርሞን መጠንን ከፍ በማድረግ የረሃብ ስሜትን ይጨምራል።
በመሆኑም በቤትም ሆነ በስራ ቦታ ውጥረትን ከሚያባብሱ ነገሮች መራቅና ባስ ያለችግር ካለም ባለሙያን ማማከር ይገባል ትላለች አንጌላ በርጌንስ።
የአዕምሮ ውጥረትን ሳያረግቡ የሚደረግ ውፍረት የመቀነስ ሩጫም ትርፉ ድካም ብቻ መሆኑንም በማከል።
7. ስፖርታዊ እንቅስቃሴን ብቸኛው መፍትሄ አድርጎ መቁጠር
ስፖርታዊ እንቅስቃሴዎች ጤናማ ያልሆነ ክብደትን ለመቀነስ ትልቅ ድርሻ እንዳለው እሙን ነው።
ነገር ግን ብቸኛው መፍትሄ አይደለም የምትለው የሰነምግብ ባለሙያዋ አንጌላ በርጌንስ፥ ጤናማ ምግብን ማዘውተር ብቻውን ውፍረትን እንደማይቀንሰው ሁሉ ስፖርታዊ እንቅስቃሴም በተናጠል ስኬታማ አያደርግም ብላ ታምናለች።
“ስፖርት እየሰራን ከላይ የተጠቀሱትን ስህተቶች ከፈጸምናቸው ምኑን ውፍረት ቀነስነው” ብላም ትሞግታለች።
8. በቂ ፕሮቲን አለማግኘት
ጤናማ ያልሆነ ክብደትን ለመቀነስ መዘንጋት የለበትም በሚል በባለሙያዋ የተጠቀሰው ፕሮቲን ያላቸውን ምግቦች የመውሰዱ ጉዳይ ነው።
“ፕሮቲን የጥጋብ ስሜትን ስለሚሰጥ አብዝቶ ከመብላት ይታደጋል፤ የምግብ መፈጨትንም ስለሚያፋጥን ያልተገባ ውፍረትን ያስወግዳል” ትላለች።
እናም እንደ እንቁላል፣ ስጋ እና አሳ ያሉ በፕሮቲን የበለጸጉ ምግቦችን መመገብን ትመክራለች።
አጠቃላይ የአመጋገብ ሂደቱ ግን እንደየሰው የደም አይነትና ሌሎች ተያያዥ ጉዳዮች ከባለሙያ ጋር በመነጋገር ሊፈጸም እንደሚገባም ነው ባለሙያዋ ያሳሰበችው።
ባለፉት 18 አመታት በስነምግብ ዘርፍ የሰራችውና ውፍረቷን አስወግዳ ሸንቃጣ አቋም የያዘችው አንጌላ በርጌንስ በኢንስታግራም ገጿ ለተከታዮቿ በየጊዜው መምሰል ምክሮችን ትለግሳለች።