ክብደት ለመቀነስ ለሰባት ሳምንት አፏን የዘጋችው ደቡብ አፍሪካዊት
14 ነጥብ 3 ኪሎ ግራም የቀነሰችው ወጣት፤ ለ50 ቀናት የተዘጋ አፏን ከፍታ መመገብ ተቸግሬያለሁ ብላለች
በአስገራሚ ድርጊቷ ትችት ቢበዛባትም ትኩረቷን አላማዋ ላይ ማድረጓ ለተመኘችው ውጤት እንዳበቃትም ተናግራለች
ከወደ ደቡብ አፍሪካ የተሰማው ዜና ለውበት የሚከፈል መስዋዕትነት ምን ላይ እንደደረሰ አሳይቷል።
አቪዌ ማዞሲዌ ከፍ ያለ ጡቷን በቀዶ ህክምና ለመቀነስ በቅድሚያ የሰውነቷ ክብደት ከቁመቷ ሊመጣጠን እንደሚገባ ይነገራታል።
በራስ መተማመኔ ከፍ ብሎ ደስተኛ ህይወትን ለመጀመር ቀዶ ህክምናው (ሰርጄሪ) መደረግ እንዳለበት ያመነችው ማዞሲዌ፥ ምግብ እየቀነሰች ክብደቷን ማስተካከል ጀመረች።
ለእለታት ከምግብ በመራቅም 12 ኪሎ ቀነሰች። ወጣቷ ይህም በቂ ሆኖ አላገኘችውም፤ ከበድ ያለ እርምጃን ወሰደች። ምንም አይነት ምግብ ወደ ጉሮሮዋ እንዳይወርድ አፏን ዘጋች።
የላይና ታች መንጋጋዎቿ እንዲጋጠሙ በጥርስ ብረት (ኦርቶዶኒክ ብራኬትስ) ግጥም አደረጋቸው ለሰባት ሳምንታት ቆየች።
የየእለት ለውጧንም በቲክቶክ ላይ ስታጋራ ሰንብታለች።
ማዞሲዌ የገጠማት ግን ከፍ ያለ ተቃውሞ ነው፤ "ቲክቶክ መጠቀም እንዳቆም የገፋፉኝ ብዙ አሉታዊ አስተያየቶች ይደርሱኛል፥ ነገር ግን የሚያበረቱኝም ነበሩ፤ ትኩረቴን ክብደት መቀነስ ላይ አድርጌ ተሳክቶልኛል" ብላለች።
ለ50 ቀናት አፏን ለምግብ ዘግታ ፈሳሽ ነገሮችን ብቻ እየወሰደች የቆየችው ወጣት፥ 14 ነጥብ 3 ኪሎግራም መቀነሷን ገልፃለች።
ክብደት መቀነሷ የጓጓችለትን የጡት ቀዶ ህክምናውን ለማድረግ ያስችላት አያስችላት ግን የተናገረችው ነገር የለም።
የሰባት ሳምንታት ልምምዴ ራስን በስነምግባር ማነፅ እና ጤናማ አመጋገብን የመከተል ቁርጠኝነትን አስተምሮኛል ያለችው አቪዌ ማዞሲዌ፥ ለምግብ ተከርችሞበት የቆየው አፏ ሲከፈት የናፈቃትን በርገር መመገብ አልቻለችም።
ተጋጥሞ የከረመ መንጋዋ ተቃንቶ ጥርሶቿም ምግብ መፍጨት ይጀምሩ ዘንድ ቀናት አስፈልገዋታል።
እንደ ማዞስዌ ላሉ ልዩ ፍላጎት ላላቸው እንስቶች የጥርስ ስፔሻሊስቶች አፍን በጥቂቱ ከፈት የሚያደርጉ መሳሪያዎችን ማስተዋወቃቸውን ጠቅሶ አስገራሚውን ዜና ኦዲቲ ሴንትራል ይዞ ወጥቷል።