ተመድ ዓለማችንን ለመታደግ ሰዎች አመጋገባቸውን እንዲያስተካክሉ አሳሰበ
በዓለማችን በየዓመቱ ከሚመረተው ምግብ ውስጥ ሲሶው ይባክናል ተብሏል
ተመድ በዓለማችን 2 ቢሊዮን ሰዎች ከመጠን በላይ ሲወፍሩ ግማሽ ሚሊዮን ያህሉ ደግሞ ከመጠን በላይ መክሳት ችግር አለባቸው ብሏል
የተባበሩት መንግስታት ድርጅት (ተመድ) ዓለማችንን ለመታደግ ሰዎች አመጋገባቸውን ማስተካከል አለባቸው ሲል አሳሰበ።
የድርጅቱ አባል አገራት መሪዎች በኒዮርክ ስብሰባቸውን በማካሄድ ላይ ናቸው።
የዚህ ስብሰባ አንድ አካል የሆነው የዓየር ንብረት ጉባኤ የተካሄደ ሲሆን የተመድ ዋና ጸሃፊ አንቶኒዮ ጉቴሬዝ ባደረጉት ንግግር “ምድራችንን ከውድመት ለመታደግ ዓመጋገባችንን ልናስተካክል ይገባል” ማለታቸውን ሲጂቲኤን አፍሪካ ዘግቧል።
“ከተፈጥሮ ጋር የገባንበትን ጦርነት ልናቆም ይገባል፤ የዓመጋገብ ስርዓታችንን ስናስተካክል ተፈጥሮ ትታረቀናለች” ሲሉም አክለዋል ዋና ጸሃፊው።
ተመድ በፈረንጆቹ 2030 ዓመት በዘላቂ ልማት ግቦች ባስቀመጠው መሰረት ከአስር ዓመት በኋላ ድህነትን ማጥፋት፤የአካባቢ ደህንነትን ማረጋገጥ እንዲሁም ዘላቂ ፍጆታን እና ምርትን ማረጋገጥ ቢሆንም የሰው ልጆች ከተፈጥሮ ጋር የገቡበት ጦርነት እቅዱ እንዳይሳካ እያደረገ ነው ተብሏል።
እቅዶቹን ለማሳካት እና ዓለማችንን ለመጠበቅ ከተፈጥሮ ጋር የተናበበ መፍትሄ እንደሚያስፈልግ በጉባኤው ላይ ተገልጿል።
የሰዎች ያልተስተካከለ አመጋገብ ወደ ከባቢ አየር ለሚለቀቀው በካይ ጋዝ አንድ ሶስተኛ ድርሻ አለው ተብሏል።
የሰው ልጅ ባስከተለው የአየር ንብረት ብክለት ምክንያት ረሀብ እንዲከሰት እና ድህነት እንዲንሰራፋ ማድረጉም ተገልጿል።
በዓለማችን 3 ቢሊዮን ሰዎች የተስተካከለ ምግብ እንደሌላቸው ተመድ በሪፖርቱ የገለጸ ሲሆን 2 ቢሊዮን ሰዎች ደግሞ ከመጠን በላይ ውፍረት ሲወፍሩ ግማሽ ሚሊዮን ሰዎች ደግሞ ከመጠን በላይ የሰውነት ክሳት ችግር አለባቸውም ብሏል።
በዓለማችን በየዓመቱ ከሚመረተው ምግብ ውስጥ አንድ ሶስተኛው የሚወገድ ሲሆን የምግብ ስርዓታችን ቢቀየር ግን ብክነቱን በማስቀረት በምግብ እጥረት ምክንያት የሚሞቱ ሰዎችን ማዳን እንደሚቻል የተመድ ሪፖርት ያስረዳል።