8ቱን የአለማችን ፈርጦች የሚያገናኘው የሩብ ፍጻሜ
ሜሲ፣ ሮናልዶ፣ ኔይማር እና ሌሎች ኮከቦች የሚፋለሙበት የኳታር የአለም ዋንጫ የሩብ ፍጻሜ ነገ ይጀመራል
አፍሪካዊቷ ሞሮኮ የሮናልዶን ሀገር አሸንፋ ግማሽ ፍጻሜውን ትቀላቀል ይሆን?
የኳታር የአለም ዋንጫ የአራት ጊዜ ሻምፒዮኗን ጀርመን፣ ቤልጂይም እና ስፔንን ጨምሮ ለዋንጫ ተጠባቂ የነበሩ ሀገራትን በምድብ እና በጥሎ ማለፉ አሰናብቶ ሩብ ፍጻሜ ላይ ደርሷል።
ስምንት ሀገራት የሚፋለሙባቸው ልብ አንጠልጣይ የሩብ ፍጻሜ ጨዋታዎችም ነገ ይጀመራሉ።
ክሮሽያ ከብራዚል፤ ኔዘርላንድስ ከአርጀንቲና የሚያደርጉት ጨዋታ የግማሽ ፍጻሜ ተፋላሚዎቹን ይለያል።
22ኛው የአለም ዋንጫ እንደ ሊዮኔል ሜሲ እና ክርስቲያኖ ሮናልዶ አይነት የአለም ኮከቦችን በምድብና በሩብ ፍጻሜ ጨዋታ አላሰናበተም።
የብራዚሉ ኔይማር፣ የፈረንሳዩ ኪሊያን ምባፔ፣ የእንግሊዙ ሃሪ ኬን፣ የክሮሺያው ሉካ ሞድሪችም ሀገራቸውን ለግማሽ ፍጻሜ ለማድረስ ሲፋለሙ የማየት እድል ገጥሞናል።
የውድድሩ ክስተት የሆነችው ሞሮኮም እንድ አሽራፍ ሃኪሚ ያሉ ፈርጦቿ ተጠባቂ ናቸው።
የአለም ዋንጫው ሩብ ፍጻሜ - የኮከቦች ፍልሚያ
1. የኬን እና ምባፔ (አንግሎ ፍሬንች) ትንቅንቅ
የአውሮፓ ብሎም የአለም እግር ኳስ ሻምፒዮኖቹ ፈረንሳይ እና እንግሊዝ ከ10 አመት በኋላ በትልቅ መድረክ የሚገናኙት የፊታችን ቅዳሜ ነው።
በዩሮ 2012 1 ለ 1 አቻ የተለያዩት ሁለቱ ሀገራት በአለም ዋንጫው ለመጨረሻ ጊዜ የተገናኙት በ1982 ነው። በወቅቱ በሚሼል ፕላቲኒ የሚመሩት ሰማያዊዮቹ የ3 ለ 1 ሽንፈት ማስተናገዳቸው ይታወሳል።
ሶስቱ አናብስት በ1966 አንድ ለናቱ የሆነውን የአለም ዋንጫቸውን ሲያነሱም ካሸነፏቸው ሀገራት መካከል አንዷ ፈረንሳይ ናት።
በሩብም ሆነ በግማሽ ፍጻሜ ጨዋታ ተገናኝተው የማያውቁት ሁለቱ ሀገራት ቅዳሜ የሚያደርጉት ጨዋታ ግን ፈረንሳይ ጎልታ የምትወጣበት እንደሚሆን ይጠበቃል።
በኳታር አምስት ጎሎችን በማስቆጠር የ2022ቱን የፊፋ የወርቅ ጫማ ሽልማት ለመውሰድ እየመራ ያለው ኪሊያን ምባፔ እና የምንጊዜም የፈረንሳይ ጎል አስቆጣሪነትን ክብር የተቀዳጀው ኦሊቨር ጂሩድ የሶስቱን አናብስት የግብ ክልል ይቆጣጠሩታል።
ምባፔ በአለም ዋንጫው በጀርመናዊው ሚሮስላቭ ክሎስ የተያዘውን የምንጊዜም ጎል አስቆጣሪ (16) ክብር ለመጎናጸፍ 8 ጎሎችን ማስቆጠር ይበቃዋል።
የዋይኒ ሩኒን የምንጊዜም የእንግሊዝ ጎል አስቆጣሪነት ክብርን (53) ለመስበር ሁለት ጎሎች ብቻ የቀሩት ሃሪ ኬን ደግሞ በእንግሊዝ በኩል ለሌላ ክብረወሰን ይጫወታል።
ኬንና የቡድን አጋሮቹ በምድብ ጨዋታ ያሳዩትን ድንቅ ብቃት ከደገሙት ለሰማያዊዮቹ ፈታኝ መሆናቸው አይቀርም።
2. ሜሲና ሮናልዶ በሉሳይል ስታዲየም በፍጻሜው ይገናኙ ይሆን?
1000ኛ ፕሮፌሽናል ጨዋታውን በዶሃ ያደረገው ሊዮኔል ሜሲም ሆነ በአምስት የአለም ዋንጫዎች ጎል ያስቆጠረው ክርስቲያኖ ሮናልዶ ወደ ሀገራቸው ትልቁን ዋንጫ በመውሰድ ታሪክ ለማጻፍ ይጓጓሉ።
ሜሲ ከአርጀንቲና ጋር ባለፈው የኮፓ አሜሪካን ዋንጫ፤ ሮናልዶ ደግሞ በ2016 የአውሮፓ ዋንጫን አንስተዋል። ነገር ግን ትልቅ ክብር የሚሰጠውን የአለም ዋንጫ ማንሳት አልቻሉም።
የ35 እና 38 አመት ተጫዋቾቹ በኳታር የአለም ዋንጫ ተሳትፏቸው ሊደመደም ይችላል መባሉም ከቀደም የአለም ሃያልነት ፉክክራቸው ጋር ተዳምሮ ማን ይሳካለት ይሆን የሚለውን ተጠባቂ አድርጎታል።
ሁለቱም ግን ሩብ ፍጻሜውን እንኳን ቢያልፉ የነኔይማርና ምባፔ ወይም ኬን ፍጥጭ ይጠብቃቸዋል።
3. ከፍጻሜ በፊት ሌላ ፍጻሜ
በሩብ ፍጻሜው ድል ከቀናቸው የደቡብ አሜሪካዎቹ ብራዚል እና አርጀንቲና በግማሽ ፍጻሜው ይፋለማሉ።
የ5 ጊዜ የአለም ዋንጫ ሻምፒዮኗ ብራዚል ከጉዳት በተመለሰው ኔይማር እየተጋዘች የምስራቅ አውሮፓዋን ሀገር ክሮሺያ የመርታት ትልቅ ግምት ተስጥቷታል።
የሜሲ ሀገር አርጀንቲናም ኔዘርላንድስን መርታት ከቻለች እንኳን ሌላ ፈተና ከፊቷ ይደቀናል፤ ሴሌሳዎቹ።
የሉካ ሞድሪቿ ክሮሽያ ግማሽ ፍጻሜውን ከተቀላቀለች ግን የደቡብ አሜሪካ ሀገራቱ ፍልሚያ ሳይሳካ ይቀራል።
የልዊስ ቫን ሃሏ ኔዘርላንድስም የዴኒስ ቤርካምፕን የሽርፍራፊ ደቂቃዎች ጎል አይነት ጀብደኛ ካገኘች አርጀንቲናን ከውድድሩ ውጭ ታደርጋለች።
አሃዞች ግን ከደቡብ አሜሪካዊቷ ሀገር ጎን ናቸው፤ አርጀንቲና በ1978 ዋንጫ ያነሳችው ኔዘርላንድስን አሸንፋ ነው። ከ8 አመት በፊት ሲገናኙም ውሃ ሰማያዊ እና ነጭ ለባሾቹ ናቸው በመለያ ምት የረቱት።
በአለም ዋንጫው ታሪክ ከማይዘነጉ ታሪኮች ውስጥ የሚነሳው ዴኒስ ቤርካምፕ በ1998ቱ የአለም ዋንጫ ባለቀ ስአት ጎል አስቆጥሮ ኔዘርላንድስ ለግማሽ ፍጻሜ ያበቃበት መንገድ አሁንም ይወሳል።
ኮዲ ጋክፖ የቤርካምፕን ተዓምር በኳታር ያሳያል ወይ? ነው ጥያቄው።
4. ልብ አንጠልጣዩዋ ሞሮኮ
ቤልጂየምን ከምድቧ ስፔንን ደግሞ ከሩብ ፍጻሜው ውጭ ያደረገችው ሞሮኮ በኳታሩ የአለም ዋንጫ ድንቅ ግስጋሴ ያደረገች ሀገር ናት።
ሩብ ፍጻሜውን በመቀላቀል ከአፍሪካ ሀገራት 4ኛ የሆነችው የሰሜን አፍሪካዋ ሀገር የተደራጀ ቡድኗ በዋሊድ ሬግራጊ እየተመራ ፖርቹጋልን ይገጥማል።
ባልፉት ሰባት ጨዋታዎች አንድ ጎል ብቻ የገባበት ብሄራዊ ቡድን በነአሽራፊ ሃኪሚ እና ሃኪም ዚያች ድንቅ ብቃት ታግዞ አፍሪካ አቀበት የሆነባትን ግማሽ ፍጻሜ ለመቀላቀል ይፋለማል።
ብዙ የተባለላትን ስፔንን ጥለው ያለፉት የአትላስ አንበሶቹ በርግጥስ በሮናልዶ የምትመራውን ፖርቹጋል ከግማሽ ፍጻሜ ውጭ ያደርጓታል? ቅዳሜ 12 ስአት ላይ የሚጀመረው ፍልሚያ መልሱን ይዟል።