በኳታር የዓለም ዋንጫው ኮኮብ ተጫዋች እና አግቢ ማን ሊሆን ይችላል?
በ6 ብሔራዊ ቡድኖች ውስጥ ያሉ ተጫዋቾች ይሄንን ሽልማት የመውሰድ እድል አላቸው ተብሏል
ምባፔ፣ ሳካ፣ ሜሲ፣ ሞረታና ጅሩድን ጨምሮ ሌሎችን ተጠባቂ ናቸው፤ በእርስዎ ግምት የወርቅ ጫማውን ማን እሚወስድ ይመስልዎታል?
በኳታር አዘጋጅነት እየተካሄደ ያለው 22ኛው የዓለም ዋንጫ ውድድር እንደቀጠለ ነው።
በዚህ ቀልብ ሳቢ ውድድር ላይ ተሳታፊ ብሔራዊ ቡድኖች ወደ ቀጣዩ ዙር ለማለፍ የሞት ሽረት ትንቅንቃቸው እንደቀጠለ ይገኛል።
አንዱ ብሔራዊ ቡድን ድል ቀንቶት ወደ ቀጣዩ ዙር በማለፉ ሲፈነጥዝ ተሸናፊው ደግሞ በተቃራኒው በሜዳ ውስጥ ሲያለቅስ ታይቷል።
የሆነው ሆኖ በዚህ ውድድር ላይ ከተሳተፉ ብሔራዊ ቡድኖች ውስጥ በተለየ መንገድ ተጽዕኖ የፈጠሩ ተጫዎቾች አሉ።
የዓለም ዋንጫውን ያሸንፋሉ ከተባሉት ብሔራዊ ቡድኖች መካከል የጀርመን ብሔራዊ ቡድን አንዱ ቢሆንም ከውድድሩ በጊዜ ተሰናብቷል።
ለመሆኑ በዘንድሮው ውድድር ላይ ለኮኮብ ተጫዋቾች እና ኮኮብ ግብ አግቢ የሚሰጠውን የወርቅ ጫማ ማን ሊወስድ ይችላል?
በስድስት ብሔራዊ ቡድኖች ውስጥ ያሉ ተጫዋቾች ይሄንን ሽልማት የመውሰድ እድል እንዳላቸው ጎል ስፖርት በድረገጹ አስነቧል
ፈረንሳዊ የ23 ዓመት ተጫዋች ክሊያን ምባፔ በዚህ ውድድር ላይ ጎልቶ የወጣ ተጫዋች ሲሆን የወርቅ ጫማ ሽልማትን ሊወስድ እንደሚችል ተጠቅሷል።
ምባፔ ሀገሩ ፈረንሳይ ባደረገቻቸው ጨዋታዎች ላይ ተሰልፎ አምስት ጎሎችን በማስቆጠር እየመራ ይገኛል።
በዚሁ ብሔራዊ ቡድን ውስጥ ያለው ሌላኛው ፈረንሳዊ ኦሊቨር ዥሩድ ሶስት ጎሎችን በማስቆጠር ለኮኮብ ግብ አግቢነት እየተፎካከረ ይገኛል።
ስፔናዊ አልቫሮ ሞራታ ደግሞ ሶስት ጎሎችን በማስቆጠር በእጩነት የተቀመጠ ሲሆን ሀገሩ በቀጣይ በምታደርጋቸው ጨዋታዎች ተጨማሪ ጎሎችን እንደሚያስቆጥር ይጠበቃል።
የእንግሊዝ ብሔራዊ ቡድን ተጫዋቾች ቡካዮ ሳካ፣ ሀሪ ኬን ፣ ጁድ ቤሊንግሀም እና ራሽፎርድ ሀገራቸው በቀጣይ በምታደርጋቸው የዓለም ዋንጫ ጨዋታዎች ላይ ተጨማሪ ጎሎችን የሚያስቆጥሩ ከሆነ የኮኮብ ግብ አግቢ ሽልማትን ሊያሸንፉ ይችላሉ ተብሏል።
የኔዘርላንዱ ኮዲ ጋክፖ ደግሞ በዚህ ውድድር ላይ ጎልቶ የወጣ ሌላኛው ተጫዋች ሲሆን እስካሁን ሶስት ጎሎችን አስቆጥሯል።
የዘንድሮው የዓለም ዋንጫ የመጨረሻው ውድድር ሊሆን ይችላል የተባለው አርጀንቲናዊው ሊዮኔል ሜሲ የዚህ ውድድር ኮኮብ ግብ አግቢ ሽልማትን እና ኮኮብ ተጫዋችነት ሽልማትን ሊያሸንፍ እንደሚችል ተገልጿል።
ፖርቹጋላዊው ብሩኖ ፈርናንዴዝ በዚህ ውድድር ላይ ደምቁው ከታዩ ተጫዋቾች መካከል አንዱ ሲሆን ጎል በማስቆጠር እና ለግብ የሆኑ ኳሶችን በማቀበል ረገድ ከቀድሚዎቹ ተርታ ተሰልፏል።