ከ800 ሺህ በላይ ዩክሬናውያን የግዳጅ ወታደራዊ ምልመላውን ሽሽት ተደብቀው እንደሚኖሩ ተነገረ
ምልመላውን የሚያደርጉት ወታደራዊ እና ፖለቲካዊ አመራሮች በአመት እስከ 2 ቢሊየን ዶላር ጉቦ እየተቀበሉ ነው ተብሏል
ወታደራዊ ምልመላውን ፍራቻ በድብቅ የሚኖሩ ወጣቶች ቁጥር መበርከት ኢኮኖሚው ላይ የአምራች ሀይል እጥረት እንዲፈጠር አድርጓል
800 ሺህ ዩክሬናውያን ሀገሪቱ ያሳለፈችውን የግድጃ ወታደራዊ አገልግሎት ምልመላ ለመሸሽ ተደብቀው እንደሚኖሩ ተነግሯል፡፡
ከሩስያ ጋር እያደረገች በምትገኘው ውግያ ከፍተኛ የወታደር እጥረት ያለባት ዩክሬን ማንኛውም እድሜ እና የጤና ሁኔታው የሚፈቅድለት ዩክሬናዊ በሙሉ በመከላከያው ውስጥ እንዲያገለግል አስገዳጅ ህግ አውጥታለች፡፡
ይህን ተከትሎም የቻሉት ከሀገር ለመውጣት የተለያዩ ጥረቶችን ሲያደርጉ ቀሪዎቹ ደግሞ በዚያው በሀገራቸው ውስጥ በዋሻ እና መሬት ውስጥ ተደብቀው እንደሚኖሩ ነው የተሰማው፡፡
ከፋይናንሻል ታይምስ ጋር ቆይታ ያደረጉት የዩክሬን ፓርላማ የኢኮኖሚ እና ልማት ጉዳዮች ኮሚቴ ሰብሳቢ ድሚትሪ ናታሉካ እንደተናገሩት በአሁኑ ወቅት ወታደራዊ ምልመላውን ፍራቻ በድብቅ የሚኖሩ ወጣቶች ቁጥር መበርከት ኢኮኖሚው ላይ የአምራች ሀይል እጥረት እንዲፈጠር እደረገ ነው፡፡
በዚህ የተነሳም በሀገሪቱ የሚገኙ ፋብሪካዎች ፣ የንግድ ሱቆች እና ሌሎችም አገልግሎቶች ለኢኮኖሚው ያላቸው አበርክቶ እየቀነሰ ሲሆን ጦርነቱ በአጠቃላይ ምጣኔ ሀብቱ ላይ ከፈጠረው ጫና ባለፈ የአምራች ሀይል እጥረት ምርት እና ምርታማነትን ወደ ኋላ የሚጎትት እንደሆነ የፓርላማ አባሉ ተናግረዋል፡፡
ከዚህ በተጨማሪ በምልመላ ስራ ላይ የሚሳተፉ ፖለቲካዊ እና ወታደራዊ አመራሮች ወጣቶችን ወደ ጦር ሜዳ ላለመላክ ከቤተሰቦቻቸው በአጠቃላይ በአመት ከ700 ሚሊየን - 2 ቢሊየን ዶላር ጉቦ እየሰበሰቡ እንደሚገኙ በጥናት መረጋገጡን አንስተዋል፡፡
ይህንን ችግር ለመቅረፍ እና በኢኮኖሚው ላይ እየደረሰ የሚገኘውን ጫና ለመከላከል አዲስ ረቂቅ ህግ የኢኮኖሚ እና ልማት ጉዳዮች ኮሚቴው ያዘጋጀ ሲሆን ፋብሪካዎች እና የንግድ ተቋማት ከአጠቃላይ ሰራተኞቻቸው 50 በመቶ ያህሉ በግዳጅ ምልመላው እንዳይመለመሉ የሚያዝ ነው፡፡
ነግር ግን ተቋማቱ ከምልመላ ለቀሩት 50 በመቶ ሰራተኞቻቸው 490 ዶላር በወር ለመንግስት መክፈል ይጠበቅባቸዋል፡፡
ይህ ረቂቅ በፓርላማው የሚጸድቅ ከሆነ ወደ 895 ሺህ የሚጠጉ ወጣቶችን ከወታደራዊ አገልግሎት የሚታደግ ሲሆን በተጨማሪም ኢኮኖሚው 4.9 ቢሊየን ዶላር ማመንጨት እንደሚችል ነው የተነገረው፡፡
በወር እስከ 50 ሺህ አዳዲስ ምልምሎች የሚያስፈልጓት ዩክሬን በዚህ አመት መጀመርያ ላይ ባስተዋወቀችው የግዳጅ ወታደራዊ አገልግሎት ህግ በአሁኑ ወቅት በወር እስከ 30ሺህ አዳዲስ ወታደሮችን እየመለመለች ትገኛለች፡፡