ማሊ ከዩክሬን ጋር ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነቷን አቋረጠች
ዩክሬን በማሊ የሚንቀሳቀሱ ጽንፈኞችን በማሰልጠን ወታደሮቼን አስገድላለች በሚል በማሊ ክስ ቀርቦባታል
በዩክሬን ሰልጥነዋል የተባሉ የተዋረግ አማጺያን ከ100 በላይ የማሊ እና ሩሲያ ቅጥረኛ ወታደሮችን ገድለዋል ተብሏል
ማሊ ከዩክሬን ጋር ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነቷን አቋረጠች፡፡
ምዕራብ አፍሪካዊቷ ማሊ ከዩክሬን ጋር ያላትን ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ማቋረጧን አስታውቃለች፡፡
ማሊ ለዚህ ውሳኔ የበቃችው በዳካር ሴኔጋል ያለው የዩክሬን ኢምባሲ በድረገጹ በሰሜናዊ ማሊ የሚንቀሳቀሱ አክራሪዎች በሩሲያ ቅጥረኛ ወታደሮች እና ማሊ ወታደሮች ላይ ጥቃት ማድረሳቸውን የሚያወድስ ይዘት ያለው መግለጫ ካሰራጨች በኋላ ነው፡፡
ኢምባሲው አክሎም ዩክሬን በማሊ በሽብርተኝነት ለተፈረጁ ተዋረግ አማጺያን ወታደራዊ ስልጠና መስጠቷን እና ወታደራዊ ድጋፍ ማድረጓን በይፋ ገልጿል፡፡
ይህን ተከትሎም የዩክሬን ድርጊት የማሊን ሉዓላዊነት የጣሰ ነው በሚል ሀገሪቱ ከኪቭ ጋር ያላትን ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት እንዳቋረጠች የማሊ ከፍተኛ ባለስልጣን የሆኑት ኮለኔል አብዱላይ ማይጋ ለቢቢሲ ተናግረዋል፡፡
ኒጀር፣ ማሊ እና ቢርኪናፋሶ ከኢኮዋስ አባልነት መውጣታቸውን አስታወቁ
እንደ ኮለኔል ማይጋ አስተያየት ከሆነ ዩክሬን በግልጽ ሽብርተኞችን በመርዳት የሀገሪቱ ወታደሮች እንዲገደሉ ድጋፍ አድርጋለች ይህ መሆኑ በጣም ያስቆጫል ብለዋል፡፡
የዩክሬን ወታደራዊ ደህንነት ቃል አቀባይ አንድሪ ዩሶቭ በበኩላቸው አማጺያኑ ስለ ድሮን ጥቃት እና ሌሎች ወታደራዊ ድጋፎች እንደተደረገላቸው ተናግረዋል፡፡
አማጺያኑ ከ10 ቀናት በፊት አደረሱት በተባለው ጥቃት 84 የዋግነር እንዲሁም 47 የማሊ ወታደሮችን አንደተገደሉ ተዋረግ የተሰኘው አማጺ ቡድን በመግለጫው ላይ መጥቀሱን በዘገባው ላይ ተጠቅሷል፡፡
በማሊ እና አልጀሪያ ድንበር አቅራቢያ ተፈጸመ የተባለው ይህ ጥቃት ከሩሲያ ጋር ጦርነት ውስጥ ያለችው ዩክሬን የመረጃ እና ጦር መሳሪያ ድጋፍ እንዳገኙ ተገልጿል፡፡