ዩክሬን አሜሪካ ሰራሽ ኤፍ-16 ጄቶችን መጠቀም ጀመረች
ፕሬዝዳንት ዜለንስኪ ጄቶቹ የሩሲያን ሚሳኤሎችና አውሮፕላኖች መትቶ ለመጣል ትልቅ ድርሻ አላቸው ብለዋል
ሩሲያ ኤፍ-16 የጦር አውሮፕላኖች መትታ እንደምትጥል የዛተች ሲሆን፥ ጄቶቹን ለሚጥሉ ወታደሮቿም ሽልማት አዘጋጅታለች
ዩክሬን አሜሪካ ሰራሽ ኤፍ-16 ጄቶችን መጠቀም መጀመሯን ፕሬዝዳንት ቮልድሚር ዜለንስኪ ተናገሩ።
ፕሬዝዳንቱ የሀገሪቱ አውሮፕላን አባራሪዎች ኤፍ-16 የውጊያ ጄቶችን ማብረር መጀመራቸው ትልቅ ድል መሆኑን በመጥቀስ ተጨማሪ ጄቶች እንዲቀርቡ ጥሪ አቅርበዋል።
ኬቭ ሩሲያ ጦርነት ካወጀችባት ጀምሮ አሜሪካ ሰራሹን ኤፍ-16 አውሮፕላን አሜሪካም ሆነች ሌሎች ጄቱን የሚጠቀሙ ሀገራት እንዲሰጧት ስትወተውት መቆየቷ ይታወሳል።
ፕሬዝዳንት ዜለንስኪ ዩክሬን ከማን እና ምን ያህል ኤፍ-16 ጄቶች እንዳገኘች አልገለጹም።
ትናንት በይፋ ሀገራቸው ጄቶቹን መጠቀም መጀመሯን በገአልጹበት መድረክ ላይ ግን አራት ጄቶች ታይተዋል (ሁለት እየበረሩ፤ ሁለት ደግሞ ቆመው)።
አሜሪካ ሰራሹ 29 ኤፍ-16 ጄት 29 ወራት ያስቆጠረውን የሩሲያ እና ዩክሬን ጦርነት አውድ እንደሚለውጥ ይጠበቃል።
የዩክሬን ጦር አዛዥ ኦሌክሳንደር ስይርስኪም ጄቶቹ የኬቭ ከተሞችን የሚደበድቡ የሩሲያን አውሮፕላኖች እና ሚሳኤሎችን መትቶ በመጣል ረገድ ትልቅ ድርሻ እንደሚኖራቸው ነው የተናገሩት።
ዩክሬን የምትጠቀማቸው የሶቪየት ሰራሽ ያረጁ የጦር አውሮፕላኖች አነስተኛ ከመሆናቸው ባሻገር አብዛኞቹ በሞስኮ ተመተው ወድመውባታል።
አሜሪካ ሰራሽ ኤፍ-16 ጄቶችን መረከቧን “አዲስ ምዕራፍ” ነው ያሉት ፕሬዝዳንት ዜለንስኪ፥ የኬቭ አጋሮች ተጨማሪ ኤፍ-16 ጄቶችን እንዲያቀርቡና የዩክሬን አብራሪዎችን እንዲያሰለጥኑ ጠይቀዋል።
ዩክሬን የተረከበቻቸው ጄቶች ምን አይነት ሚሳኤሎችን መተኮስ እንደሚችሉ አለመጠቀሱን ተከትሎ በጦር ግንባር የሚኖራቸው ፋይዳን ለመገመት አስቸጋሪ አድርጎታል።
የዩክሬን የጦር አውሮፕላኖች የተከማቹባቸውን ስፍራዎች ደጋግማ የደበደበችው ሩሲያ በበኩሏ አዳዲሶቹን ኤፍ-16 ጄቶች መትታ እንደምትጥል መዛቷን ሬውተርስ አስነብቧል።
ክሬምሊን ባለፈው ሳምንት ባወጣው መግለጫ ሮኬቶች፣ ሚሳኤሎች እና ቦምቦችን መሸከም የሚችሉት አሜሪካ ሰራሽ ጄቶች በውጊያው ላይ የጎላ ተጽዕኖ እንደማይኖራቸው አመላክቷል።
ሞስኮ ኤፍ-16 ጄቶችን መትተው ለሚጥሉ ወታደሮቿ መጠኑን ባትጠቅሰውም ሽልማት ማዘጋጀቷንም የክሬምሊን ቃል አቀባይ ዲሚትሪ ፔሶቭ መናገራቸው የሚታወስ ነው።