ሩሲያ ለኢራን የአየር መቃወሚያዎች እና ራዳሮች መላክ መጀመሯ ተነገረ
የሩሲያ የደህንነት ምክርቤት ዋና ጸሃፊው ሰርጌ ሾጉ በቴህራን ከኢራኑ ፕሬዝዳንት መሱድ ፔዝሽኪያን ጋር ተወያይተዋል
ሩሲያ የሃማስ የፖለቲካ መሪ ኢስማኤል ሃኒየህ ግድያን አጥብቃ ማውገዟ ይታወሳል
ሩሲያ ወደ ኢራን የአየር መቃወሚያ እና ራዳሮችን መላክ መጀመሯ ተነገረ።
ቴህራን የመካከለኛው ውጥረት ባየለበት ወቅት አጋሯ ሞስኮ የአየር መቃወሚያ እንድትልክላት በይፋ መጠየቋን የሀገሪቱ ባለስልጣናት እንዳረጋገጡለት ኒውዮርክ ታይምስ ጋዜጣ አስነብቧል።
በትናንትናው እለት የሩሲያው የደህንነት ምክርቤት ዋና ጸሃፊና የቀድሞው የመከላከያ ሚኒስትር ሰርጌ ሾጉ በቴህራን ያደርጉት ጉብኝትም ከዚሁ ጋር የተያያዘ ነው ተብሏል።
ሰርጌ ሾጉ ከአዲሱ የኢራን ፕሬዝዳንት መሱድ ፔዝሽኪያን ጋር መክረዋል።
በዚህ ምክክርም ፕሬዝዳንት ፔዝሽኪያን ኢራን ቀጠናዊ ጦርነት እንዲጀመር ባትፈልግም “እስራኤል ለፈጸመችው ወንጀልና ትዕቢት ዋጋዋን እንድታገኝ ማድረጋችን አይቀሬ ነው” ማለታቸውን የኢራን መገናኛ ብዙሃን ዘግበዋል።
ሩሲያም የሃማስ የፖለቲካ መሪ ኢስማኤል ሃኒየህ ግድያን ካወገዙት ሀገራት መካከል ቀዳሚዋ ናት።
ሾጉ ከኢራኑ ፕሬዝዳንት ጋር ባደረጉት ውይይት ስለሃኒየህ ግድያ እና ስለእስራኤልና ኢራን ውጥረት ያሉት ነገር ባይጠቀስም ሀገራቸው ከኢራን ጋር “በሁሉም ዘርፎች ትተባበራለች” ብለዋል።
ሞስኮ የቴህራን እና ቴል አቪቭ ፍጥጫ ባየለበት ወቅት የአየር መቃወሚያዎችን እና ራዳሮችን መላኳም የሀገራቱ ትብብር ማሳያ ተደርጎ ተወስዷል።
የእስራኤል አጋር አሜሪካ ተጨማሪ አውሮፕላን ተሸካሚ መርከቦች እና የጦር ጄቶች እልካለሁ ባለች ማግስት ሩሲያ ከኢራን ጋር መተባበሯ ቀጠናውን የሃያላኑ መሻኮቻ ሊያደርገው ይችላል ተብሏል።
እስራኤል ዛሬ ወይም ነገ ኢራን ጥቃት ልትሰነዝር ትችላለች መባሉን ተከትሎ በተጠንቀቅ ላይ እንደምትገኝ ታይምስ ኦፍ እስራኤል ዘግቧል።
የሀገሪቱ መከላከያ ሚኒስትር ዮቭ ጋላንት የቴህራንን ጥቃት ለመመከት ዝግጁ መሆን እንደሚገባ አሳስበዋል።