8 ሺህ የሚጠጉ የሰሜን ኮሪያ ወታደሮች “በጥቂት ቀናት ውስጥ” ዩክሬንን መውጋት ይጀምራሉ - አሜሪካ
የሩሲያን ወታደራዊ መለዮ የለበሱት የሰሜን ኮሪያ ወታደሮች በሩሲያና ዩክሬን ድንበር ላይ እንደሚገኙ ፔንታጎን አስታውቋል
ዩክሬን በሩሲያ የሚገኙ የሰሜን ኮሪያ ወታደሮችን ቁጥር 12 ሺህ አድርሳዋለች
በዩክሬን ድንበር የሚገኙ 8 ሺህ የሚጠጉ የሰሜን ኮሪያ ወታደሮች በጥቂት ቀናት ውስጥ ወደ ውጊያ ግንባሮች እንደሚገቡ አሜሪካ ገለጸች።
የአሜሪካ የመከላከያ እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች ከደቡብ ኮሪያ አቻቸው ጋር በትናንትናው እለት በዋሽንግተን መክረዋል።
የተወሰኑት የሩሲያ ወታደሮችን መለዮ የለበሱት የሰሜን ኮሪያ ወታደሮች ኩርክስ ክልል ውስጥ መግባታቸውንና በጥቂት ቀናት ውስጥ ለሩሲያ መዋጋት እንደሚጀምሩ ነው የአሜሪካ መከላከያ ሚኒስትር ሊዩድ ኦስቲን የተናገሩት።
የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ አንቶኒ ብሊንከንም ሩሲያ የሰሜን ኮሪያ ወታደሮችን በድሮን አጠቃቀምና በሌሎች የውጊያ ዘዴዎች ዙሪያ ስታሰለጥን መሰንበቷን መናገራቸውን ፍራንስ 24 ዘግቧል።
አሜሪካ በሩሲያ የሚገኙ የሰሜን ኮሪያ ወታደሮች ቁጥር 10 እንደሚደርስ ገልጻለች። ደቡብ ኮሪያ እና አጋሮቿ ደግሞ ቁጥሩን ወደ 11 ሺህ ከፍ ያደርጉታል። ዩክሬን በአንጻሩ አሃዙን 12 ሺህ አድርሳዋለች።
የደቡብ ኮሪያው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ቾ ታይ ዩል የሰሜን ኮሪያ ወታደሮች ከሩሲያ በፍጥነት እንዲወጡ አሳስበዋል።
አሜሪካ እና ደቡብ ኮሪያ በትናንቱ ምክክራቸው የፒዮንግያንግ ወታደሮች በዩክሬን ጦርነት መሳተፍ የሩሲያ ዩክሬን ጦርነትን ከማራዘም ባሻገር የእስያ ፓስፊክ ቀጠና ውጥረትን ያባብሳል ብለዋል።
ቻይና የተደቀነውን ቀተናዊ አደጋ በመገንዘብ የፒዮንግያንግ ወታደሮች ከሩሲያ እንዲወጡ እንድታደርግም ነው የጠየቁት።
ሩሲያ በዩክሬን ጦርነት ከጀመረች ወዲህ ለኬቭ 59 ቢሊየን ዶላር የሚገመት ወታደራዊ ድጋፍ ያደረገችው ዋሽንግተን በቅርቡ ተጨማሪ ድጋፍ ይፋ እንደምታደርግ አስታውቃለች።
አሜሪካ እና ደቡብ ኮሪያ የሚኒስትሮች ምክክር በጀመሩበት እለት ሰሜን ኮሪያ ከአንድ አመት በኋላ አህጉር አቋራጭ ባለስቲክ ሚሳኤል ሞክራለች።
ፒዮንግያንግ የሚሳኤል ሙከራዋ እንዲሳካ ከሞስኮ የቴክኖሎጂ ድጋፍ ሳይደረግላት እንዳልቀረ ተገምቷል።
ምዕራባውያን በዚህ ወር በ1 ሺህ ኮንቴነሮች የተጫኑ የጦር መሳሪያዎችን በባቡር ወደ ሩሲያ ልካለች ያሏት ሰሜን ኮሪያ በምትኩ ከሞስኮ ስላገኘችው ድጋፍ በዝርዝር አልጠቀሱም።