ሰሜን ኮሪያ ሩሲያን ለመርዳት ወታደሮቿን ብትልክ ህጋዊ እርምጃ እንደሚሆን ገለጸች
ዩክሬን ሰሜን ኮሪያ ሞስኮ የጀመረችውን ጦርነት የምትቀላለቀል ከሆነ በአለምአቀፍ ህግ መሰረት ወረራ እንደፈጸመች ተደርጎ ይቆጠራል ብላለች
ዩክሬን፣ አሜሪካ እና ሌሎች ምዕራባውያን አጋሮቿ ፒዮንግያንግ በዩክሬን የሚሳተፉ ወታደሮችን ወደ ሩሲያ መላኳን የሚያሳይ መረጃ እንዳላቸው ገልጸዋል
ሰሜን ኮሪያ ሩሲያን ለመርዳት ወታደሮቿን ብትልክ ህጋዊ እርምጃ እንደሚሆን ገለጸች።
ሰሜን ኮሪያ በዩክሬኑ ጦርነት ሩሲያን ለመርዳት ወታደሮቿን ብታሰማራ አለምአቀፍ ህግን ያከበረ እርምጃ እንደሚሆን ገልጻለች።ነገርግን ሰሜን ኮሪያ ወታደሮቿን ማስማራቷን አላረጋገጠችም።
ዩክሬን፣ አሜሪካ እና ሌሎች ምዕራባውያን አጋሮቿ ፒዮንግያንግ በዩክሬን ጦርነት ከሩሲያ ጎን ሆነው የሚሳተፉ በሺዎች የሚቆጠሩ ወታደሮችን ወደ ሩሲያ መላኳን የሚያሳይ መረጃ እንዳላቸው ገልጸዋል።
ቀደም ሲል ፒዮንግያንግ እና ክሬሚሊን አንዲህ አይነት ሪፖርቶች አሉባልታ ናቸው ሲሉ አጣጥለዋቸው ነበር። ነገርገን ባለፈው ሀሙስ ስለእነዚህ ሪፖርቶች የተጠየቁት የሩሲያው ፕሬዝደንት ፑቲን ሪፖርቶቹን በግልጽ አላስተባበሉም።
ዩክሬን ሰሜን ኮሪያ ሞስኮ በየካቲት 2022 የጀመረችውን ጦርነት የምትቀላለቀል ከሆነ በአለምአቀፍ ህግ መሰረት ወረራ እንደፈጸመች ተደርጎ ይቆጠራል ብላለች።
የሰሜን ኮሪያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ኪም ጆንግ ግዩ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መከላከያ ሚኒስቴርን በሚመለከቱ ጉዳዮች ላይ በቀጥታ እንደማይሳተፍ መናገራቸውን ሮይተርስ ኬሲኤንኤን ጠቅሶ ዘግቧል።
ነገርግን ግዩ አክለው እንዳሉት "የአለም ሚዲያ የሚያወራው እውነት ከሆነ፣ እኔ እንደሚመስለኝ አለምአቀፍ ህግን ያከበረ ነው።"
ሰሜን ኮሪያ እና ሩሲያ የዩክሬኑ ጦርነት ከተጀመረ ወዲህ ወታደራዊ ስምምነት በመፈራረም ጭምሮ ግንኙነታቸውን አጠናክረዋል። ዩክሬን እና ምዕራባውያን ሀገራት ሰሜን ኮሪያ ለሩሲያ የጦር መሳሪያ እያቀረበች ነው የሚል ክስ ሲያቀርቡባት ቆይተዋል። ነገርግን ፒዮንግያንግ እና ሞስኮ የምዕራባውያንን ክስ ሀሰት ነው ሲሉ አስተባብለዋል።
ፕሬዝደንት ፑቲን ባለፈው ሀሙስ እለት የሰሜን ኮሪያን ወታደሮች መጠቀም ወይም ያለመጠቀም ጉዳይ የሞስኮ ነው ብለዋል። ፑቲን ምዕራባውያንን የዩክሬኑን ጦርነት እያባባሱት ነው ሲሉ ከሰዋል።
የዩክሬኑ ፕሬዝደንት ቮሎድሚር ዘለንስኪ ባለፈው አርብ እለት ሩሲያ የሰሜን ኮሪያ ወታደሮችን ከጥቅምት 27-28 ባለው ጊዜ ውስጥ ወደ ጦር ሜዳ ልታሰማራ መሆኑን የሚያሳይ የደህንነት መረጃ እንዳላቸው ተናግረዋል።
የዩክሬን ደህንነት እንደሚለው ከሆነ 500 ኦፊሰሮችን እና ሶሰት ጀነራሎችን ጨምሮ 12ሺ የሰሜን ኮሪያ ወታደሮች ሩሲያ ውስጥ በአምስት ቦታዎች ሰልጥነው ዝግጁ ሆነዋል።
አሜሪካ እና ደቡብ ኮሪያም የሰሜን ኮሪያ ወታደሮች ሩሲያ ውስጥ መግባታቸውን መረጃ እንዳላቸው ገልጸዋል ።