ደቡብ ኮርያ በዩክሬን ጦርነት ለመዋጋት በሩሲያ ይገኛሉ የተባሉ የሰሜን ኮርያ ወታደሮች በፍጥነት እንዲወጡ ጠየቀች
ከሰሞኑ ቁጥራቸው 1500 የሚጠጉ የሰሜን ኮርያ ወታደሮች ወደ ሩስያ መግባታቸውን የሚሳዩ የሳተላየት ምስሎች በሰፊው ሲሰራጩ ነበር
የውጭ ሀገር ጦር በጦርነቱ በቀጥታ መሳተፍ ሶስተኛው የአለም ጦርነትን የሚያስከትል የመጀመርያው ውሳኔ ስለመሆኑ እየተነገረ ነው
ደቡብ ኮሪያ በዩክሬን ጦርነት ለሩሲያ ወግነው ለመዋጋት ተልከዋል የተባሉ የሰሜን ኮርያ ወታደሮች በአፋጣኝ ሩሲያን ለቀው እንዲወጡ ጠየቀች፡፡
ከሰሞኑ በዋና ዋና መገናኛ ብዙሀን እና በማህበራዊ ትስስር ገጾች የሰሜን ኮርያ ወታደሮች እንደሆኑ የተገለጹ የታጠቁ ወታደሮች በሩሲያ መታየታቸውን የሚያሳይ ተንቀሳቃሽ ምስል እና የሳተላየት ፎቶ በሰፊው ሲዘዋወር ታይቷል፡፡
ደቡብ ኮሪያ በሴኡል የሚገኙ የሩሲያ አምባሳደርን በመጥራት ዩክሬን ውስጥ ለመዋጋት በሩሲያ እየሰለጡኑ ነው ያለቻቸው የሰሜን ኮሪያ ወታደሮች በአስቸኳይ ለቀው እንዲወጡ ጠይቃለች፡፡
የደቡብ ኮሪያ ምክትል የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ኪም ሆንግ ክዩን ከአምባሳደሩ ጆርጂ ዚኖቪየቭ ጋር ባደረጉት ውይይት ድርጊቱን አውግዘው ሀገራቸው እርምጃ ልትወሰድ እንደምትችል አስጠንቅቀዋል።
ምክትል የውጭ ጉዳይ ሚንስትሩ አክልውም ስጋቱ የደቡብ ኮሪያ ብቻ ሳይሆን የአለምአቀፉ ማህበረሰብም ጭምር ስለሆነ ለጉዳዩ ትኩረት እንዲሰጠው ጠይቀዋል፡፡
የሩሲያ አምባሳደር ዚኖቪየቭ በበኩላቸው ስጋቶቹን ለመንግስት እንደሚያስተላልፉ ተናግረው በሞስኮ እና በፒዮንግያንግ መካከል ያለው ትብብር በአለም አቀፍ ህግ ማዕቀፍ ውስጥ መሆኑን አፅንዖት ሰጥተዋል፡፡
ሞስኮ እና ፒዮንግያንግ የተፈራረሙትን የመግባብያ ስምምነት ተከትሎ የሰሜን ኮሪያ ጦር በዩክሬን እየተዋጋ እንደሚገኝ የተለያዩ ማሳያዎችን በማንሳት ደቡብ ኮሪያ መረጃዎችን ስታወጣ ሰንብታለች፡፡
በተጨማሪም ሁለቱ ሀገራት ከፍተኛ የጦር መሳሪያ ድጋፍ ልውውጥ እንዳላቸው ስትወቅስ የቆየችው ደቡብ ኮርያ አሁን ያለው ሁኔታ ግን ወታደራዊ ቁሳቁሶችን ከማዘዋወር ያለፈ ነው ትላለች፡፡
ክሪምሊን ከሴኡል እና ዩክሬን በሰሜን ኮርያ ወታደሮች ዙርያ የሚቀርብበትን ክስ በተደጋጋሚ ሀሰተኛ ዜና እንደሆነ በመግለጽ ሲያስተባብል ቆይቷል፡፡
የልዩ ሃይል ወታደሮችን ጨምሮ 1,500 የሚጠጉ የሰሜን ኮሪያ ወታደሮች ሩሲያ መግባታቸውን የሴኡል የስለላ ድርጅት መረጃ ያመላክታል፡፡
የመንግስት ባለስልጣናትን በምንጭነት የሚጠቅሱ አንዳንድ የደቡብ ኮሪያ ሚዲያዎች ደግሞ እስከ 12,000 የሚደርሱ የሰሜን ኮሪያ ወታደሮች በቀጣይ ሊሰማሩ እንደሚችሉ ጠቁመዋል።
ትብብራቸውን እያጠናከሩ የሚገኙት ሞስኮ እና ፒዮንግያንግ መሪዎቻቸው ቭላድሚር ፑቲን እና ኪም ጆንግ ኡን በሰኔ ወር የመከላከያ ስምምነት ከተፈራረሙ በኋላ በሁለቱም ሀገራት ላይ ጥቃት በሚፈጠርበት ጊዜ እርስ በርስ ለመረዳዳት ቃል ገብተዋል፡፡
ባለፈው ሳምንት ፕሬዝዳንት ፑቲን ስምምነቱ የሚጸድቅበትን ረቂቅ አስተዋውቀዋል።
ሰሜን ኮሪያ ከሩሲያ ጎን ሆና ለመፋለም ወታደሮቿን ማሰማራቷ በግጭቱ ውስጥ ትልቅ ለውጥ ያመጣል ያሉት የኔቶ ዋና ጸሃፊ ማርክ ሩት የውጭ ሀገር ጦር በጦርነቱ በቀጥታ መሳተፍ ሶስተኛው የአለም ጦርነትን የሚያስከትል የመጀመርያው ውሳኔ ነው ብለዋል፡፡
ሰሜን ኮሪያም ሆነች ሩሲያ እስካሁን ጉዳዩ እውነት አለመሆኑን እየተናገሩ ይገኛሉ፡፡