የሰሜን ኮሪያን ጦር መጠቀም እና ያለመጠቀም ጉዳይ የእኛ ውሳኔ ነው - ፕሬዝዳንት ፑቲን
የዩክሬኑ ፕሬዝዳንት ሞስኮ የሰሜን ኮሪያ ወታደሮችን ከእሁድ ጀምሮ በጦር ግንባሮች ማሰማራት ትጀምራለች ብለዋል
3 ሺህ የሚጠጉ የሰሜን ኮሪያ ወታደሮች በሩሲያ እንደሚገኙ የተለያዩ መረጃዎች እየወጡ ነው
ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን የሰሜን ኮሪያ ወታደሮችን መጠቀም እና ያለመጠቀም የሩስያ ጉዳይ ነው ሲሉ በዛሬው እለት መናገራቸው ተሰምቷል፡፡
ዩክሬን የኔቶ አባል ለመሆን ያላትን ፍላጎት እስከገፋችበት ድረስ ሞስኮ የራሷን ደህንነት ለማስጠበቅ የምትፈልገውን ማድረግ ትችላለች ብለዋል ፕሬዝዳንቱ።
ፕሬዝዳንቱ ከሩሲያ መንግስት ቴሌቪዥን ጋር በነበራቸው ቆይታ፤ “ዩክሬን ከኔቶ ጋርም ሆነ ከኔቶ ውጭ ደህንነቷን እንዴት እንደምታረጋግጥ የምትወስነው ራሷ ዩክሬን ናት በሚል ደጋግመው የሚናገሩት ምዕራባውያን ከሩሲያ ጋር ባለው ግንኙነት እንዲህ አይነቱ አካሄድ ከንቱ መሆኑን በቶሎ ሲገነዘቡ ለሁሉም ሰው የተሻለ ይሆናል” ሲሉ ተደምጠዋል፡፡
3 ሺህ የሰሜን ኮርያ ጦር በሩሲያ እንደሚገኝ መረጃዎችን አግኝተናል ያለችው አሜሪካ በበኩሏ ሁነቱ የዩክሬን ጦርነት እየተባባሰ መሆኑን አመላካች እንደሆነ ከትላንት በስቲያ አስታውቃለች፡፡
የዩክሬን ወታደራዊ መረጃ አገልግሎት እንደገለጸው በሩሲያ ውስጥ የሰለጠኑ የመጀመሪያዎቹ የሰሜን ኮሪያ ጦር አባላት የዩክሬን ኃይሎች በነሀሴ ወር ጥቃት በከፈቱበት በኩርስክ ክልል ውስጥ ተሰማርተዋል፡፡
የስለላ ድርጅቱ አሜሪካ ካወጣችው የሰሜን ኮርያ ወታደሮች ቁጥር ጋር የተለያየ መረጃ ነው ያወጣው፡፡
በመረጃው መሰረትም በአሁኑ ወቅት 12 ሺህ የሰሜን ኮርያ ጦር አባላት 500 ከፍተኛ ወታደራዊ አዛዦች እና 3 ጄነራሎች በአምስት የሩሲያ ካምፖች ውስጥ የተለያዩ ስልጠናዎችን እየወሰዱ ይገኛሉ ነው ያለው፡፡
የዩክሬኑ ፕሬዝዳንት ቮልደሚር ዘለንስኪ በበኩላቸው በሀገሪቱ የስላለ ድርጅቶች መረጃ መሰረት ሩሲያ የሰሜን ኮሪያን ጦር ከመጪው እሁድ እና ሰኞ ጀምሮ በዩክሬን የውግያ ግንባሮች ለማሰማራት አቅዳለች ብለዋል።
ፑቲን በሰኔ ወር በፒዮንግያንግ ባደረጉት ጉብኝት ከሰሜን ኮሪያው መሪ ኪም ጆንግ ኡን ጋር ሁሉን አቀፍ ስትራቴጂካዊ አጋርነት ስምምነት ተፈራርመዋል፡፡
በዚህ ስምምነት አንቀጽ 4 ላይ ከሁለቱ ሀገራት በአንደኛው የትኛውም ክልል ወይም ግዛቶች ጥቃት ከተፈፀመ እና ጦርነት ውስጥ ከገባ ሌላኛው ወገን በማንኛውም መንገድ ወታደራዊ እና ሌሎች ድጋፎችን እንደሚያደርግ ያስቀምጣል፡፡