"አርበኞቻችን እንዳሳዩን የድል ሚስጥሩ ጀግንነት እና እንደ ሀገር አብሮ መቆም ነው"- ፕሬዝዳንት ሣህለወርቅ
81ኛው የጀግኖች አርበኞች ድል ቀን በዓል ተከብሯል
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ቀደምት ዐርበኞች ላከበሯት ሀገራችን ልዕልናና ብልጽግና ዋጋ የምንከፍል ተተኪ ዐርበኞች እንሁን ሲሉ ጥሪ አቅርበዋል
81ኛው የኢትዮጵያ አርበኞች የድል ቀን በዓል ተከበረ፡፡
በዓሉ ፕሬዝዳንት ሳህለ ወርቅ ዘውዴ፣ የኢትዮጵያ ጀግኖች አርበኞች ማህበር ፕሬዝዳንት ልጅ ዳንኤል መስፍን ጆቴ እንዲሁም ሌሎች አባት አርበኞችና ባለስልጣናት በተገኙበት በአዲስ አበባ አራት ኪሎ ድል ሃውልት ስር የአበባ ጉንጉን በማስቀመጥና በተለያዩ ስነ ስርዓቶች ተከብሯል፡፡
በአከባበር ስነ ስርዓቱ የተለያዩ ሃገራት አምባሳደሮችና የዲፕሎማቲክ ማህበረሰቡ አባላት ተገኝተዋል፡፡
በስነ ስርዓቱ ላይ "አርበኞቻችን እንዳሳዩን የድል ሚስጥሩ ጀግንነት እና እንደ ሀገር አብሮ መቆም ነው" ሲሉ ንግግር ያደረጉት ፕሬዚዳንት ሣህለወርቅ ዘውዴ ኢትዮጵያውያን መነጋገር ፣ መግባባት እና አቅጣጫን አስተካክሎ መራመድ እንደሚኖርባቸው ገልጸዋል፡፡
ጀግኖችን ሲዘከሩ ሌሎች በርካታ ጀግኖችን ለማፍራት ቆርጦ በመስራት ሊሆን ይባዋልም ብለዋል ፕሬዚዳንት ሣህለወርቅ፡፡
"ዐርበኝነት ማለት በሀገር ጉዳይ ላይ ለእውነትና ለእምነት የሚከፈል መሥዋዕትነት ነው" ሲሉ በዓሉን የተመለከተ የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክትን ያስተላለፉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ በበኩላቸው የሀገራቸውን ነጻነትና ሉዓላዊነት ለመጠበቅ ሲሉ ምትክ የሌለውን ሕይወታቸውን የከፈሉ ኢትዮጵያውያን ጀግኖች እናትና አባቶች በክብር የሚታሰቡበት ቀን መሆኑን ገልጸዋል።
"እኛም ልጆቻቸው፣ ቀደምት ዐርበኞች ላከበሯት ሀገራችን ልዕልናና ብልጽግና ለማጎናጸፍ ዋጋ የምንከፍል ተተኪ ዐርበኞች መሆናችንን ልናረጋግጥ ይገባናል"ም ነው ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ በመልዕክታቸው ያሉት።
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን በበኩላቸው ጀግኖች አርበኞች ለሃገር አንድነት እና ሉዐላዊነት መከበር የከፈሉትን ዋጋ በትውልዱ ዘንድ ተምሳሌታዊ የድል አድራጊነት መንፈስ እንዲጋባ በማሰብ ሊዘከር እንደሚገባው በማስታወስ የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።
"እንደሃገር የገጠሙንን ፈተናዎች በፅናት በመሻገር ለመጪው ትውልድ ነፃ፣ ሰላማዊ እና የበለፀገች ኢትዮጵያን ለማውረስ ዳር እስከዳር አንድነታችንን ማጥበቅ እና መጠበቅ ይገባናል"ም ብለዋል በጋራ እንቁም ሲሉ የአደራ መልዕክት ያስተላለፉት አቶ ደመቀ።
በዓሉ ኢትዮጵያውያን ጀግኖች አርበኞች ለዳግም ወረራ ከመጣው የፋሽስት ጣሊያን ወራሪ ሃይል ጋር ለአምስት ዓመታት ያህል በዱር በገደሉ ተዋድቀው ያስመዘገቡትን ደማቅ ለማሰብ የሚከበር ነው፡፡
ይህን በማስመልከትም ዛሬ ማለዳ አስራ ሁለት ሰዓት ላይ 21 ጊዜ መድፍ መተኮሱ ይታወሳል፡፡
በ1928 ዓ/ም ወደ ኢትዮጵያን ዳግም ለመውረር የመጣው የፋሽስት ጦር በ1933 ዓ/ም ተመልሶ መውጣቱም አይዘነጋም፡፡