ጠቅላይ ሚኒስትሩ ዛሬ ከዳውሮ ማህበረሰብ አባላትና ነዋሪዎች ጋር መክረዋል
በአሁኑ ሰዓት የሚያስፈልገው ጀግንነት በአንድነት ሆኖ ግድቡን ማጠናቀቅ ነው
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ዛሬ ከዳውሮ ማህበረሰብ አባላትና ነዋሪዎች ጋር መክረዋል፡፡
ታለቁን የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ጨምሮ በተለያዩ ርዕሰ ጉዳዮች አስተያየታቸውን የሰጡት ጠቅላይ ሚኒስትሩ “በአሁኑ ሰዓት የሚያስፈልገው ጀግንነት በአንድነት ሆኖ ታላቁን የሕዳሴ ግድብ ማጠናቀቅ ነው” ብለዋል፡፡
የድህነትን ከፋፋይነት ባነሳ ንግግራቸውም ግድቡ ከኢትዮጵያ አልፎ ለጎረቤቶቿ የኃይል ምንጭ እንዲሆን የማድረግ ዓላማ እንዳለው ነው የተናገሩት፡፡
የጠቅላይ ሚኒስትሩን ጥረት ያደነቁት የውይይቱ ተሳታፊዎች ከመጠጥ ውኃ፣ከኤሌክትሪክ ኃይል አቅርቦት እና ከተጀመሩ የመንገድ ግንባታዎች መጠናቀቅ ጋር በተያያዘ አሉብን ያሏቸውን ችግሮች አንስተዋል፡፡
በተጨማሪም፣ የዳውሮ ቅርሶች እንዲመዘገቡ ደማድረግ እንቅስቃሴ እንዲጀመር፣ የኦሞ ሸለቆ እሴቶች ላይ የሚያተኩር ጥናት እና ምርምር እንዲካሄድ እና የቀርከሃ ኢንደስትሪ ተፈጥሮ ለሥራ ዕድል እንዲውልም ተጠይቋል።
ለተነሱት ጉዳዮች ምላሽ የሰጡት ጠቅላይ ሚኒስትሩ የሀገር በቀል ኢኮኖሚ ማሻሻያው እና በቅርቡ የሚጀመረው የ10 ዓመት ብሔራዊ ዕቅድ ቁልፍ ይዘቶች በዳውሮ ነዋሪዎች የተነሱትን ጥያቄዎች በተሟላ መልኩ ለመመለስ የሚያስችል አካሄድ እንዳላቸው ገልጸዋል።