የ82 ዓመቷ እናት ሲመኙች የኖሩትን ዲግሪ ለማሳካት በ70 ዓመታቸው ወደ ትምህርት መመለሳቸውን ተናግረዋል
በአሜሪካ ሜሪላንድ የሚገኘው የሜሪላንድ ዩኒቨርሲቲ ግሎባል ካምፓስ ከሰሞኑ ለየት ያሉ ተመራቂን በማስተናገዱ የበርካቶችን ቀልብ ሊስብ ችሏል።
ይህም የ82 ዓመት እድሜ ባለፀጋ አዛውንት የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን (ባችለርስ ዲግሪ) ከዩኒቨርሲቲው መቀበላቸው እንደሆነ ዩ.ፒ.አይ ይዞት በወጣው ዘገባው አስታውቋል።
ማዔ ቤያል የተባሉት የ82 ዓመቷ አዛውንት ሲመኙት የኖሩትን ዲግሪ በዩኒቨርሲቲው የምረቃ ስነ ስርዓት መድረክ ላይ ወጥተው ተቀብለዋል።
ለረጅም ዓመታት በነርስነት እንዳገለገሉ የሚናገሩት ቤያል፤ ሲያልሙት የኖሩትን ዲግሪ ለማሳከት በ70 ዓመታቸው ወደ ትምህርት ቤት ተመልሰው መግባታቸውን ይናገራሉ።
ትምህርታውን በመከታተልም ለዩኒቨርሲቲ የበቁት አዛውንቷ ቤያል፤ ለሚሰሩት የሁነት ዝግጅት (event planning) ያግዘኛል ያሉትን ቢዝነስ ማናጅመንት ትምህርት መምረጣቸውን ተናግረዋል።
በዚህም የሜሪላንድ ዩኒቨርሲቲ ግሎባል ካምፓስ በቢዝነስ ማናጅመንት የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን ባለፍነው ረቡዕ መቀበል ችለዋል።
“አማካሪዎቼ የሆነ የተለየ ነገር እንዳለኝ ያስባሉ” ያሉት የ82 ዓመቷ አዛውንት ቤያል፤ “በህክምና ስራ ላይ እያለሁ ትላልቅ ሁነቶችን አዘጋጅ ነበረ፤ ሁሉም ሰው ስራዬን ሲያ ይገረማል” ብለዋል።
አዛውንቷ ቤያል፤ ሁነት ማዘጋጀት የጀመሩት የሚሰሩበትን ድርጅት የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ኮንፈረንስ እንደሆነ ያስታውሳሉ።
አሁን የተማሩት የቢዝነስ ማናጅመንት ትምህርትም የሁነት አዘጋጅነት ስራቸውን ለማሳደግ እንደሚረዳቸውም ተናግረዋል።
ማዔ ቤያል የ82ኛ ዓመት የልደት በዓላቸውን ማከሰኞ እለት እክበረው፤ በማግስቱ ረቡዕ እለት ዲግሪያቸውን እንደተቀበሉም ተነግሯል።
በትልቅ እድሜ ከፍተኛ ትምህርት ተቋምን መቀላቀል አሁን አሁን በኢትዮጵያም እየተሰማ ከመጣ ዋል አደር እያለ ሲሆን፤ ከወር በፊት የ69 ዓመት አዛውንት አቶ ታደሰ ድንቃ ጅማ ዩኒቨርሲቲን መቀላቀላቸው ይታወሳል።
በተመሳሳይ ባሳለፍነው ሳምንትም ይመኙሽ ምትኩ የተባሉ የ47 ዓመት እናት ወለጋ ዩኒቨርሲቲን መቀላቀላቸው ይታወሳል።