“እስካሁን የተገደሉ ሰዎችን አስክሬን ማንሳት አልቻልንም“ - የምዕራብ ወለጋ አካባቢ ነዋሪዎች
በአንድ ቦታ ብቻ 135 ሰዎች መቀበራቸውንም የዐይን እማኞች ገልጸዋል
አስክሬን ለመቅበር “እስካቫተር ቢዘጋጅም ባለስልጣናት “ስማችን ይጠፋል” በማለታቸው በዶማ እንዲቆፈር ታዟልም ብለዋል ነዋሪዎቹ
ከሰሞኑ በኦሮሚያ ክልል የተገደሉ ዜጎችን አስክሬን ማንሳት አለመቻሉን የአካባቢው ነዋሪዎች ለአል ዐይን አማርኛ ገለጹ፡፡
ዜጎቹ የተገደሉት በኦሮሚያ ክልል ምዕራብ ወለጋ መሆኑን የገለጹት ነዋሪዎቹ አሁንም ከፍተኛ የጸጥታ ስጋት እንዳለ ተናግረዋል፡፡ በኦሮሚያ ክልል ምዕራብ ወለጋ ዞን ጊምቢ ወረዳ በሚገኙ ሶስት ቀበሌዎች ላይ ጥቃት መፈጸሙን የተናገሩት አቶ ኢብራሂም ሁሴን (ስማቸው ለዚህ ዘገባ የተቀየረ) ናቸው፡፡
አቶ ኢብራሂም እንዳሉት ጥቃቱ የተጀመረው ሰኔ 11 ቀን ከጠዋቱ 3 ሰዓት ጀምሮ እስከ 7 ሰዓት ነው፡፡ጥቃቱ ከተፈጸመባቸው ሶስት ቀበሌዎች አንዷ በሆነችው ቶሌ ቀበሌ አምስት ጎጦች ውስጥ በርካታ ዜጎች ተገድለዋል፡፡ ከ2 ሺ 500 በላይ አባወራዎች በሚኖርባቸው በሁሉም ጎጦች ላይ ግድያ መፈጸሙንም ነው ነዋሪው የተናገሩት፡፡
ከቶሌ ቀበሌ ባለፈም ሳኒ እና ቂርቆሽ በሚባሉ ሌሎች ቀበሌዎች ተመሳሳይ ጥቃት ተፈትሞ በርካቶች መገደላቸውን አቶ ኢብራሂም ተናግረዋል፡፡
ሌላዋ ከጥቃት እንደተረፈች የገለጸችው አስተያየት ሰጭ ወ/ሮ ጀሚላ ሃሰን (ለዚህ ዘገባ ሲባል ስሟ የተለወጠ) አሁን ላይ በጥቃቱ ህይወታቸው ያለፈ ዜጎች አስክሬን ሙሉ ለሙሉ አለመነሳቱን ለአል ዐይን አማርኛ ገልጻለች፡፡
ሌላው ስማቸው እንዲገለጽ ያልፈለጉ የጊምቢ ወረዳ ነዋሪ በዜጎች ላይ ግድያ የተፈጸመው በጨቆርሳ፤ በጃተማ፤ በጉትን፣ በበገኔና በሀያው (ድደማ) ጎጦች መሆኑን ገልጸዋል፡፡
ከጥቃቱ የተረፉና አስተያየታቸውን ለአል ዐይን አማርኛ የሰጡት ነዋሪዎች፤ ጥቃቱ የብሔር ማንነትን መሰረት ያደረገ ነው ብለዋል፤ የሞቱት ግለሰቦች የአማራ ብሔር ተወላጅ መሆናቸውንና ጥቃቱ መደጋገሙን በመጠቆም፡፡
አስተያየት ከሰጡ የአካባቢው ነዋሪዎች መካከል አንዲት ሴት መገደሏንም ሌላኛው አስተያየት ሰጭ ተናግረዋል፡፡
ነዋሪዎቹ እስካሁን ለማንሳት ያልቻልነው አስክሬን አለ ያሉ ሲሆን አስክሬን ለመቅበር “እስካቫተር“ እንዲመጣ ጠይቀው “እምቢ” ከመባላቸው በላይ “በራሳችን አቀረብን“ ያሉትን እስካቫተር “በዓለም አቀፍ ደረጃ ስማችን ይጠፋል” ባሉ የመንግስት አካላት ትዕዛዝ መከልከላቸውን ተናግረዋል፡፡
በኦሮሚያ ክልል በምትገኘው ስልሳው ወይም ጃተማ ጎጥ ውስጥ ብቻ 135 ሰዎች በአንድ አካባቢ መቀበራቸውን የገለጹት እማኞቹ፤ በሌላ የቀብር ስፍራ ደግሞ 50 ሰዎች አንድ ቦታ ተቀብረዋል ሲሉ ነው የተናገሩት፡፡
ግድያ በተፈጸመባቸው ቦታዎች ላይ የፌደራል የጸጥታ ኃይል ማለትም መከላከያ እና ፌዴራል ፖሊስ ቢሰማራም አሁንም አስክሬን ሙሉ ለሙሉ አለመነሳቱን ተናግረዋል፡፡
አቶ ኢብራሂም በአካባቢው የፌዴራል የፀጥታ ሃይል እንዲሰማራ በተደጋጋሚ ተጠይቆ ቢሰማራም ሊታደጋቸው እንዳልቻለ ግን ገልጸዋል፤ ሊፈተሸ እንደሚገባ በማንሳት፡፡
ከሰሞኑ የኦሮሚያ ልዩ ኃይል የአካባቢውን ነዋሪዎች መሳሪያ እንዲያስረክቡ አድርጎ እንደነበር የተናገሩት ሌላው አስተያየት ሰጪ አቶ መሐመድ ኡስማን ይህንን ማድረግ ሕዝቡን ለገዳይ አሳልፎ መስጠት እንደሆነ ለአል ዐይን አማርኛ ገልጸዋል፡፡
አል ዐይን አማርኛ የኦሮሚያ ክልል የኮሙኒኬሽንና የጸጥታ ሥራ ኃላፊዎችን ለማናገር ጥረት ቢያደርግም የሥራ ሃላፊዎቹ ስልክ ባለማንሳታቸው ሃሳባቸውን ማካተት አልቻለም፡፡ ኃላፊዎቹን ባገኘ ወይም ለመመለስ በቻሉበት በማንኛውም ጊዜ የሚያስተናግድ ይሆናል፡፡
ጥቃቱን አውግዘው መግለጫ ያወጡት የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን)፣ እናት እና የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትህ (ኢዜማ) ፓርቲዎች የዜጎችን ደህንነት መጠበቅ የመንግስት ተቀዳሚ ተግባር መሆኑን በማስታወስ መነግስት ኃላፊነቱን እንዲወጣና ተጠያቂነት እንዲሰፍን ጠይቀዋል፡፡
በጥቃቱ የሸኔ ታጣቂ ቡድንን ተጠያቂ ያደረገው የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ቡድኑ ህግ በማስከበር ላይ ባሉ የመንግስት የጸጥታ ኃይሎች እየደረሰበት የሚገኘውን ከፍተኛ ሽንፈት ለመሸፈን የጥፋት በትሩን ወደ ንጹሃን በማዞሩ በኦሮሚያ ክልል ምእራብ ወለጋ ዞን ጊምቢ ወረዳ ነዋሪ የሆኑ በርካታ ንጹሃን መቀጠፋቸውን ገልጿል፡፡
እንዲህ ዐይነቱ የንጹሃን ጥቃት ተቀባይነት እንደሌለው የገለጹት የብልጽግና ፓርቲ ፕሬዝዳንት እና የሀገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የምንታገሰው አይደለም ሲሉ መግለጻቸው ይታወሳል፡፡