በ1 ሳምንት ውስጥ በሊቢያ የባህር ዳርቻ ላይ ከ880 ባላይ ስደተኞችን ከሞት እትርፌያለሁ- አይ.ኦ.ኤም
ስደተኞች ሜዲትራኒያን ባህርን አቋርጠው ወደ አውሮፓ ለመግባት ሊቢያን ሲመርጡ ይስተዋላል
አይ.ኦ.ኤም በ2021 ብቻ 30 ሺህ 990 ስደተኞች ከሞት ለማትረፍ እንደተቻለም ገልጿል
ባለፈው ሳምንት ብቻ 880 በላይ ስደተኞችን ከሊቢያ የባህር ዳርቻ ከሞት ማትረፍ መቻሉን አለም አቀፍ የስደተኞች ድርጅት /አይ.ኦ.ኤም/ አስታወቀ፡፡
በፈረንጆቹ ከህዳር 21 እስከ 27 2021 በነበሩ ጊዜያት 886 ስደተኞች ታድነው ወደ ሊቢያ ተመልሰዋል”ም ነው ያለው ድርጅቱ።
ድርጅቱ በ2021 ብቻ እስካሁን ሴቶችና ልጆች የሚገኙባቸው 30 ሺህ 990 ስደተኞች ከሞት ለማትረፍ እንደተቻለም ነው የገለጸው።
ድርጅቱ አክሎም “506 ስደተኞች ባህር ለማቋረጥ ሲመክሩ ህይወታቸው አልፏል” ያለ ሲሆን 807 ስደተኞች ደግሞ መጥፋቸውንም አስታውቋል።
እንደፈረንጆቹ በ2011 ሟቹ መሪ ሙአመር ጋዳፊ ከወደቁ በኋላ ሀገሪቱ ከነበረችበት አለመረጋጋት እና የፀጥታ ሁኔታ አንፃር፤በርካታ አፍሪካውያን ስደተኞች ሜዲትራኒያን ባህርን አቋርጠው ወደ አውሮፓ የባህር ዳርቻዎች ለመዝለቅ ሊቢያን ሲመርጡ ይስተዋላል።
እነዚያን ማዕከላት ለመዝጋት ተደጋጋሚ ዓለም አቀፍ ጥሪ ቢደረግም፤ አሁንም ስደተኞች በመላ ሊቢያ በተጨናነቁ የእስር ማቆያ ማዕከላት ውስጥ እንደሚገኙ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የህጻናት ፈንድ (ዩኒሴፍ) መረጃዎች ያመለክታሉ።
የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የህጻናት ፈንድ (ዩኒሴፍ) በሊቢያ የስደተኞች ማቆያ እስር ቤቶች የሚገኙ ከ1 ሺህ በላይ ሴቶችና ህጻናት “በአስጊ ሁኔታ ላይ” መሆናቸውን የገለጸው ከወር በፊት ነበር።
ዩኒሴፍ በወቅቱ ባወጣው መግለጫው በወርሃ ጥቅምት ብቻ በሊቢያ 255 ህጻናትን ጨምሮ 751 ሴቶች ስደተኞችና እና ጥገኝነት ፈላጊዎች በእስር ቤቶች ታጉረው ይገኛሉ ብሏል።
ዩኒሴፍ በመግለጫው “የሴቶቹና ህጻናት ደህንነት አደጋ ላይ ነው” ሲልም አስጠንቅቋል፡፡
አል-ማባኒ እስር ቤት በሊቢያ ካሉ የአስር ማቆያ ማእከላት ትልቁ ሲሆን በውስጡ መያዝ ከሚችለው አራት እጥፍ በላይ የሚሆኑ 5 ሺህ ስደተኞች ታጉረው የሚገኙበት ስፍራ ነው እንደ ዩኒሴፍ ገለጻ።