90 በመቶ አሜሪካዊያን በሀገራቸው የፖለቲካ ግጭት ይከሰታል ብለው እንደሚያምኑ ጥናት አመለከተ
በአዲሱ 2023 ዓመት የሰራተኞች አመጽ፣ የዋጋ ንረት፣ አሜሪካ በዓለም መድረክ ላይ ያላት ተሳትፎም ይቀንሳል ተብሏል
አሜሪካዊያኑ ሩሲያ በዓለም ላይ ያላት ሀይል ይቀንሳል ብለው እንደሚያምኑም ጥናቱ ጠቁሟል
90 በመቶ አሜሪካዊያን በአዲሱ ዓመት የፖለቲካ ግጭት ይከሰታል ብለው እንደሚያምኑ አንድ ጥናት አመለከተ።
ዋና መቀመጫውን አሜሪካ ያደረገው ጋሉፕ የተሰኘው የጥናት እና ምርምር ተቋም ባወጣው ሪፖርት በአዲሱ የ2023 ዓመት በአሜሪካ የፖለቲካ ግጭቶች ይከሰታሉ ብለው እንደሚያምኑ ይፋ አድርጓል።
ተቋሙ በጥናቱ እንደጠቀሰው ከ10ሩ አሜሪካዊያን ዘጠኙ በአዲሱ ዓመት የፖለቲካ ግጭት እንደሚከሰት ያምናሉ።
72 በመቶ አሜሪካውያን ደግሞ በዚሁ አዲሱ ዓመት ወንጀል ይጨምራል ብለው የሚያምኑ ሲሆን የሰራተኞች አመጽ እና ሌሎችም አለመረጋጋቶች እንደሚከሰቱ ጠቁመዋል።
ከአስር አሜሪካዊያን መካከልም ስምንቱ በዚሁ ዓመት የኢኮኖሚ ችግሮች ያጋጥመናል ብለው ያስባሉም ተብሏል።
በዚህ ጥናት ከተሳተፉት ውስጥም 60 በመቶዎቹ አሜሪካ በግብር ከፋዮች መቀነስ ምክንያት የበጀት እጥረት እንደሚገጥማት፣ የአክስዮን ገበያ እንደሚቀንስ እና ሌሎች የኢኮኖሚ ችግሮች ይከሰታሉ ብለው እንደሚጠብቁም ተገልጿል።
በአጠቃላይ ከአሜሪካ ግዙፍ የፖለቲካ ተቋማት መካከል ዲሞክራቶች በአንጻራዊነት አሜሪካ የተሻለ ዓመት ይኖራታል ብለው ሲያምኑ ሪፐብሊካኖች ግን አሜሪካ የውስጥ ፖለቲካዋ እና ኢኮኖሚዋ ይሻሻላል ብለው እንደሚያምኑ በጥናቱ ላይ ተጠቅሷል።
የሁለቱም ፓርቲዎች አባላት ሩሲያ በዓለም መድረክ ላይ ያላት ሀይል ይቀንሳል ብለው የሚያምኑ ሲሆን አሜሪካ በዓለም መድረክ ላይ በሚኖራት ሀይል ላይ ግን ተቃራኒ ትንበያዎችን አራምደዋል።