ሩሲያ በዩክሬን አዲስ ወታደራዊ ጥቃት በመሰንዘር ላይ መሆኗ አሜሪካ እንዳሳሰባት ገልጻለች
አሜሪካ የሩሲያ እና ቻይና ጥምረት እንዳሳሰባት ገለጸች።
ለሁለት ሳምንት በሚል የተጀመረው የሩሲያ-ዩክሬን ጦርነት ከተጀመረ 10 ወራትን ያስቆጠረ ሲሆን ጦርነቱ የዓለምን ምግብና ነዳጅ ዋጋ ከማናር ባለፈ የዲፕሎማሲ ትርምስንም ፈጥሯል።
በአሜሪካ አና የአውሮፓ ህብረት የሚመራው ቡድን ሩሲያን ከተቀረው ዓለም ለመነጠል ብዙ ማዕቀቦችን እና ትብብሮችን ሲፈጥሩ ሩሲያም ከአሜሪካ እና ምዕራባዊያን ጋር ሆደና ጀርባ ከሆኑ ሀገራት ጋር በመቀናጀት አዲስ ጥምረትን በመፍጠር ላይ ትገኛለች።
የዚህ አንድ አካል የሖነው የሩሲያ እና ቻይና ወዳጅነት አንዱ ሲሆን መሪዎቹ በተደጋጋሚ በአካል እና በበይነ መረብ እየተገናኙ በመምከር ላይ ናቸው።
የሩሲያ ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን እና የቻይና አቻቸው ሺ ዢ ፒንግ በትናንትናው ዕለት በበይነ መረብ አማካኝነት ባደረጉት ውይይት በቀጣዮቹ ወራት በአካል ለመገናኘት መስማማታቸውን ሮይተርስ ዘግቧል።
የቻይናው ፕሬዝዳንት በቀጣዮቹ የበጋ ወራት ውስጥ ወደ ሞስኮ በማቅናት ከፕሬዝዳንት ፑቲን ጋር በሁለትዮሽ፣ አካባቢያዊ እና ዓለም አቀፋዊ ጉዳዮች ዙሪያ ለመምከር መስማማታቸው ተገልጿል።
ይህንን ተከትሎም የአሜሪካ የምንጊዜም ተቀናቃኛ የሆኑት እነዚህ ሁለቱ ሀገራት መሪዎች በተደጋጋሚ መገናኘት እንዳሳሰባት አስታውቃለች።
እንደ አሜሪካ ውጪ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አስተያየት ከሆነ ቻይና በሩሲያ እና ዩክሬን ጦርነት ጉዳይ ገለልተኛ መሆኗን በተደጋጋሚ ብታሳውቅም ድርጊቷ ግን ያንን አያሳይም ብላለች።
በተለይም ሩሲያ በዩክሬን የጀመረችውን ጦርነት ታቆማለች በሚል በምትጠበቅበት በአሁኑ ወቅት ሞስኮ አዲስ እና ተጨማሪ የሚሳኤል ጥቃቶችን በመሰንዘር ላይ መሆኗንም ቃል አቀባዩ ተናግረዋል።
ቻይና የሩሲያ ዋነኛ የንግድ እና ኢንቨስትመንት ሸሪክ ስትሆን ከዩክሬን ጦርነት በኋላ የሁለቱ ሀገራት ንግድ እና ትብብር መጨመሩ አሜሪካ እንዳሳሰባት አስታውቃለች።
በአሜሪካ የሚመራው የቡድን ሰባት ሀገራት የሩሲያ ነዳጅ በበርሜል ከ60 ሺህ ዶላር በላይ እንዳይሸጥ ቢስማሙም ሩሲያ ስምምነቱን ለተቀበሉ ሀገራት ነዳጅ እንዳትሸጥ የሚከለክል ህግ ማውጣቷ ይታወሳል።