የአሜሪካና ቻይና የጦር ጄቶች ለጥቂት ከግጭት መትረፋቸው ተገለጸ
ክስተቱ የተፈጠረው የአሜሪካ የጦር አውሮፕላን በደቡባዊ ቻይና ባህር አቅራቢያ በመብረር ላይ እያለ እንደሆነ ተገልጿል
የአሜሪካ እና ቻይና የጦር አውሮፕላኖች ርቀታቸው የሶስት ሜትር ብቻ ነበር ተብሏል
የአሜሪካ እና ቻይና የጦር ጄቶች ለጥቂት ከግጭት መትረፋቸው ተገለጸ።
የዓለም ሁለቱ ልዕለ ሀያላን ሀገራት አሜሪካ እና ቻይና ግንኙነታቸው በየጊዜው እየተካረረ የመጣ ሲሆን ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ደግሞ መካረሩ እየባሰበት መጥቷል።
የታይዋን ጉዳይ፣ የደቡባዊ ቻይና ባህር፣ የዩክሬን ጦርነት እና የንግድ እና ቴክኖሎጂ ፉክክር ሁለቱ ሀገራት እርስ በርሳቸው የሚፎካከሩባቸው ጉዳዮች ናቸው።
ከሰሞኑ ደግሞ የሑለቱ ሀገራት የጦር አውሮፕላኖች በአየር ላይ በመብረር ላይ እያሉ ከመጋጨት ለጥቂት መትረፋቸውን ሮይተርስ ዘግቧል።
እንደ ዘገባው ከሆነ የአሜሪካው አርሲ-135 የተሰኘው የጦር አውሮፕላን በደቡባዊ ቻይና ባህር አካባቢ በመብረር ላይ እያለ ቅኝት እያደረገ የነበረው የቻይናው ጄ-11 የውጊያ አውሮፕላን ቀርቦት እንደነበር ተገልጿል።
የቻይናው የጦር ጄት የአሜሪካውን የውጊያ አውሮፕላን በቅርብ ሆኖ ተከትሎታል የተባለ ሲሆን የሁለቱ አውሮፕላኖች ርቀት ሶስት ሜትር ብቻ እንደነበርም ተጠቅሷል።
የአሜሪካ ጦር ቃል አቀባይ በጉዳዩ ዙሪያ በሰጡት መግለጫ የአሜሪካ የጦር አውሮፕላን ዓለም አቀፍ የአየር ክልልን ተጠቅሞ በመብረር ላይ እያለ የቻይና ጦር አውሮፕላን ተጠግቶት ሲበር እንደነበር ተናግረዋል።
ክስተቱ ለግጭት የሚዳርግ እና ሌሎች ጉዳቶችን የማስከተል አደጋ እንዳለው የጠቀሱት ቃል አቀባዩ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ቻይና አደገኛ የሆኑ በረራዎችን እያደረገች እንደሆነም አክለዋል።
የአሜሪካ የባህር ላይ እና የአየር ላይ ተዋጊ አውሮፕላኖች ቻይና የግሌ ናቸው ወደ ምትላቸው ደቡባዊ የቻይና ባህር አካባቢ ቅኝት ያደርጋል።
ቻይና በበኩሏ ደቡባዊ የቻይና ባህር የግሌ ንብረት እንጂ የማንም አይደሉም ፣ወደዚህ አካባቢም እንቅስቃሴ በሚያደርጉ ሀገራት ላይ እርምጃ እወስዳለሁ ስትል አስጠንቅቃለች።
ፊሊፒንስ ፣ቬትናም እና ጃፓን ቻይና የግሌ ነው በምትለው ደቡባዊ የእስያ ባህር አካባቢ ላይ የባለቤትነት ጥያቄዎችን ሲያነሱ ይሰማሉ።