ሩሲያ ከሰባት ዓመት በፊት በክሪሚያ ጉዳይ ከቡድን ስምንት ሀገራት አባልነት መታገዷ ይታወሳል
ሩሲያ ከጸጥታው ምክር ቤት እንድትባረር አሜሪካ ጠየቀች፡፡
ዩክሬን የሰሜን አትላንቲክ ቃል ኪዳን ጦር ወይም ኔቶን በአባልነት እቀላቀላለሁ ማለቷን ተከትሎ ነበር ከሩሲያ ጋር ወደ ይፋዊ ጦርነት ያመሩት፡፡
ከ10 ወር በፊት የተጀመረው ይህ ጦርነት ዩክሬንን በቀጥታ ለዜጎቿ ሞት፣ ስደት፣ መሰረተ ልማት ውድመት እና ለኢኮኖሚ ድቀት ሲዳርግ ሩሲያንም በተመሳሳይ በመጉዳት ላይ ይገኛል፡፡
ከዚህ በተጨማሪም ይህ ጦርነት ዓለምን ለሁለት በመክፈል ለዓለም ምግብና ነዳጅ ዋጋ መናር ምክንያት ከመሆኑ በተጨማሪ በአውሮፓ የነዳጅ እጥረት እንዲከሰት አድርጓል፡፡
ዓለማችን የተሻለ የጸጥታ ሁኔታ እንዲፈጠር ከሚሰሩ የዓለማችን ተቋማት መካከል ዋነኛው የሆነው የመንግስታቱ ድርጅት የጸጥታው ምክር ቤት አንዱ ነው፡፡
የዚህ ምክር ቤት አባል ከሆኑት መካከል አንዷ የሆነችው ሩሲያ በዩክሬን ጦርነት መጀመሯን ተከትሎ ከዚህ ምክር ቤት እንድትባረር አሜሪካ መጠየቋ ተገልጿል፡፡
እንደ ሮይተርስ ዘገባ የአሜሪካ ሁለት የህግ አውጪ ምክር ቤት አባላት ሩሲያ ከጸጥታው ምክር ቤት አባልነት እንድትሰረዝ፣ ሚናዋ እንዲገደብ አልያም ሌሎች እርምጃዎች እንዲወሰድባት የሚጠይቅ ህግ ማርቀቃቸው ተሰምቷል፡፡
የህግ አውጪ ምክር ቤት አባላቱ ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን ሩሲያ ከምክር ቤቱ በምትታገድበት ሁኔታ ላይ እንዲገፉበት እና ሌሎች ጫናዎችን እንዲያደርጉም ጠይቀዋል፡፡
ሩሲያ ሉዓላዊት ሀገር በሆነችው ዩክሬን ላይ በይፋ ጦርነት መጀመራቸው የመንግስታቱ ድርጅትን መርህ የሚጥስ ነው የምትለው አሜሪካ በዚህ ምክንያት ሞስኮ ከዚህ ምክር ቤት አባልነት እንድትታገድ ጥረቶች መጀመራቸውም ተገልጿል፡፡
በተጨማሪም አሜሪካ ሩሲያ ከሌሎች የተመድ ተቋማት አባልነት እንድትታገድ ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን አጋር ሀገራትን እና ተቋማትን እንዲጠቀሙም ተጠይቀዋል፡፡
ይሁንና የጸጥታው ምክር ቤት አንዷ አባል የሆነችው እና የሞስኮ ቁልፍ አጋር ቻይና ይሄንን የአሜሪካ የውሳኔ ሀሳብ ድምጽን በድምጽ የመሻር መብትን ተጠቅማ ውድቅ ልታደርገው እንደምትችል ተገልጿል፡፡
ሩሲያ በፈረንጆቹ 2014 ላይ በወቅቱ የዩክሬን አንድ አካል የነበረችው ክሪሚያ በህዝበ ውሳኔ ወደ ግዛቷ መጠቅለሏን ተከትሎ ከቡድን ስምንት አባል ሀገራት መታገዷ ይታወሳል፡፡