በ68 አመታቸው የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን ያገኙት አዛውንት “በየትኛውም አጋጣሚ መማሬን እቀጥላለሁ” ብለዋል
የ90 አመቷ አዛውንት በአሜሪካ የኖርዝ ቴክሳስ ዩኒቨርሲቲ የመመረቂያ ጽሁፋቸውን በማጠናቀቅ የማስተስር ዲግሪያቸውን ተቀብለዋል።
በዩኒቨርሲቲው ታሪክ በእድሜ የገፉት የማስተርስ ምሩቅ ሚኔ ፓይኔ ይባላሉ።
በፈረንጆቹ 1950 የሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን ያጠናቀቁት ፓይኔ ለ30 አመታት በቃላት አራሚነት እና ድምጽን ወደ ጽሁፍ በመለወጥ የስራ ዘርፍ ሰርተዋል።
እድሜያቸው 68 አመት ሲደርስም ወደ ቴክሳስ የሴቶች ዩኒቨርሲቲ በማምራት ሶስት የጋዜጠኝነት እና ቢዝነስ ኮርሶችን መውሰዳቸውን ይናገራሉ።
“ረጅም ጊዜ ከቃላት ጋር የተያያዙ ስራዎችን ሰርቻለሁ፤ ሁሌም መጻፍ ያስደስተኛል፤ እናም ራሴን ለማሳደግ ወደ ትምህርት ቤት ተመለስኩ” የሚሉት አዛውንቷ፥ ከ17 አመት በፊት የመጀመሪያ ወይም ባችለር ዲግሪያቸውን አግኝተዋል።
በዚህም በቴክሳስ ለሚገኙ ጋዜጦች በጊዜያዊ ወይም ፍሪላንስ ጸሃፊነት ለአመታት ሲሰሩ መቆይታቸውን ያወሳሉ።
የአዛውንቷ የመማር ፍላጎት በመጀመሪያ ዲግሪ ላይ ሳይቆም ወደ ኖርዝ ቴክሳስ ዩኒቨርሲቲ በመግባት በጋዜጠኝነት የማስተስር ዲግሪ መማር ጀመሩ።
ይሁን እንጂ አብዛኞቹ የጋዜጠኝነት ኮርሶች በአካል መማርን ስለሚያስገድዱ በበይነ መረብ መከታተል ወደሚችሉት ተዛማች ትምህርት ለውጠውት ትምህርታቸውን ቀጠሉ።
በዩኒቨርሲቲው የፓይኔን የመመረቂያ ጽሁፍ የሚያማክሯቸው ቢሊ ሮስለር፥ “ብዙ ጊዜ የህይወት ዘመን ተማሪ የሚለውን ቃል እንጠቀማለን፤ ይህ አገላለጽ በ90 አመታቸው የማስተርስ ዲግሪያቸውን ለመስራት በቁርጠኝነት ለተጉት ፓይኔ ይስማማል” ብለዋል።
አዛውንቷ ትምህርታቸውን ማጠናቀቅ ከሚገባቸው ጊዜ በመጠኑ ቢዘገዩም ህልማቸውን አሳክተውት በ”ኢንተርዲሲፕሊነሪ ስተዲስ” የማስተርስ ዲግሪያቸውን ተቀብለዋል።
በዚህ ግን የሚቆሙ አይመስልም፤ “በየትኛውም አጋጣሚ መማሬን እቀጥላለሁ” ሲሉም ተደምጠዋል ሲል ዩናይትድ ፕረስ ኢንተርናሽናል ዘግቧል።