ልዩልዩ
በኮፕ28 ጉባኤ ለመሳተፍ 9 ሺህ ኪሎሜትሮችን በብስክሌት የተጓዙት ጀርመናዊ
13 ሀገራትን ያቆራረጡት የ64 አመቱ ሚሸል ኤቨርትዝ ዱባይ ለመድረስ 222 ቀናት ፈጅቶባቸዋል
አዛውንቱ በጉዟቸው ስለትብብርና ወዳጅነት መልዕክት አስተላልፈዋል
በ28ኛው የመንግስታቱ ድርጅት የአየር ንብረት ለውጥ ጉባኤ ለመሳተፍ 9 ሺህ ገደማ ኪሎሜትሮችን በብስክሌት የተጓዙት ጀርመናዊ ዱባይ ገብተዋል።
ሚሸል ኤቨርትዝ የተባሉት የ64 አመት አዛውንት ከበርሊን ተነስተው ዱባይ ለመግባት 222 ቀናት ፈጅቶባቸዋል።
ሚሼል በዱባይ እየተካሄደ በሚገኘው የኮፕ28 ጉባኤ ለመሳተፍ የ13 ሀገራትን ድንበር ማለፍ ነበረባቸው።
8 ሺህ 862 ኪሎሜትሮችን በብስክሌታቸው የተጓዙት የ64 አመቱ አዛውንት አለምን እየፈተኗት ለሚገኙ ጉዳዮች የትብብርን አስፈላጊነት መልዕክት ማስተላለፋቸውን ለስካይኒውስ አረብኛ ተናግረዋል።
“የአየር ንብረት ለውጥ፣ ረሃብ እና ግጭት የምድራችን ፈታኝ ጉዳዮችን በጋራ ተባብረን ልናልፋቸው ይገባል”ም ነው ያሉት።
ሚሼል ኤቨርትዝ በዱባይ እየተካሄደ ከሚገኘው የኮፕ28 ጉባኤ በኋላ በግብጽ እና ማዕከላዊ አፍሪካ አድርገው ደቡብ አፍሪካ ጫፍ ለመድረስ አቅደዋል።
ኤቨርትዝ 30 ሀገራትን በብስክሌት ለማቆራረጥ ውጥን ይዘዋል፤ 30 ሺህ ኪሎሜትሮችን የሚረዝመው ጉዞ 800 ቀናት እንደሚወስድባቸው ይጠበቃል።
በዚህ ጉዞቸውም “በጋራ ካልቆምን እንወድቃለን” የሚል መልዕክት እንደሚያስተላልፉ ነው የገለጹት።