ከተኩስ አቁም ስምምነቱ ወዲህ 1545 እርዳታ የጫኑ ተሽከርካሪዎች ጋዛ መግባታቸውን ኦቻ ገለጸ
የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ዋና ጸሃፊ አንቶኒዮ ጉቴሬዝ የሰብአዊ ድጋፍ ዝርፊያን ለማስቆም ህግና ስርአት መከበር አለበት ብለዋል

የእስራኤልና ሃማስ ተኩስ አቁም ዛሬ ሶስተኛ ቀኑን የያዘ ሲሆን፥ ሃማስ የፊታችን ቅዳሜ አራት ታጋቾችን እንደሚለቅ አስታውቋል
የመንግስታቱ ድርጅት የሰብአዊ ጉዳዮች ማስተባበሪያ (ኦቻ) በትናንትናው እለት ብቻ 915 እርዳታ የጫኑ ተሽከርካሪዎች ጋዛ መግባታቸውን አስታወቀ።
ኦቻ የእስራኤል መንግስት እና የተኩስ አቁም ስምምነቱ አደራዳሪዎች (አሜሪካ፣ ኳታር እና ግብጽ) መረጅን ጠቅሶ ባወጣው መግለጫ እሁድ እለት 630 ተሽከርካሪዎች ጋዛ ደርሰዋል ብሏል። ከዚህ ውስጥም 300 የሚጠጉት ከፍተኛ ሰብአዊ ቀውስ ወደተከሰተበት ሰሜናዊ ጋዛ መጓዛቸውንም በማከል።
እስራኤልና ሃማስ የተፈራረሙት የተኩስ አቁም ስምምነት በየእለቱ 600 እርዳታ የጫኑ ተሽከርካሪዎች ወደ ጋዛ መግባት እንዳለባቸው አስቀምጧል። 50 የነዳጅ ቦቴዎችም ወደ ሰርጡ እንዲገቡ ያዛል።
በተመድ የፍልስጤም የእርዳታ ኤጀንሲ (UNRWA) መረጃ እንደሚያሳየው በታህሳስ ወር 2024 2 ሺህ 892 እርዳታ የጫኑ ተሽከርካሪዎች ወደ ጋዛ ሰርጥ ገብተዋል። ሰብአዊ ድጋፉ በጋዛ ድንበር ላይ ከተራገፈ በኋላ በመንግስታቱ ድርጅትና ሌሎች ተቋማት ስርጭቱ ይከናወናል።
ይሁን እንጂ በየቀኑ 72 እርዳታ የጫኑ ተሽከርካሪዎች በዘራፊዎች ባዷቸውን ቀርተው ወደመጡበት እንደሚመለሱ ኦቻ ገልጿል።
የመንግስታቱ ድርጅት ዋና ጻሃፊ ኣአንቶኒዮ ጉቴሬዝ እስራኤልና ሃማስ ተኩስ አቁመው ሰብአዊ ድጋፍ እየገባ ቢሆንም "አሰቃቂ" ሲሉ የገለጹትን ሰብአዊ ቀውስ ለመቀነስ በቂ አለመሆኑን ተናግረዋል።
ጉቴሬዝ ትናንት በጸጥታው ምክርቤት ባደረጉት ንግግር ተመድ፣ የእርዳታ ድርጅቶችና የግሉ ዘርፍ ለፍልስጤማውያን በፍጥነት እንዲደርሱ የተጋረጡ ፈተናዎች ሊቀረፉ ይገባል ነው ያሉት።
ከቪዛ እና ሌሎች የእንቅስቃሴ ፈቃዶች ጋር በተያያዘ ያሉ ማነቆዎች እንዲፈቱና እስራኤልና ሃማስ በሰብአዊ ስራዎች ላይ ውጤታማ ትብብር እንዲያደርጉም ጥሪ ማቅረባቸውን ሬውተርስ ዘግቧል።
"የሰብአዊ ድጋፍ ዝርፊያን ለማስቆም ህግና ስርአት መከበር አለበት" ያሉት የተመድ ዋና ጸሃፊ፥ ሀገራት አስቸኳይ ህክምና የሚያስፈልጋቸውን ፍልስጤማውያን ከጋዛ አስወጥተው እንዲያሳክሙም ጠይቀዋል።
በሌላ በኩል በመጀመሪያው ምዕራፍ የተኩስ አቁም ስምምነት ጅማሮ ሶስት ታጋቾችን የለቀቀው ሃማስ ቀጣዮቹን አራት ታጋቾች የፊታችን ቅዳሜ እንደሚለቅ አረጋግጧል።
የሃማስ የእስረኞች ሚዲያ ቢሮ ሃላፊ ናሄድ አል ፋኩሪ አራቱ ታጋቾች እሁድ ይለቀቃሉ ቢሉም ለሬውተርስ አስተያየታቸውን የሰጡ የሃማስ ከፍተኛ አመራር ታጋቾቹ በስምምነቱ መሰረት ቅዳሜ ይለቀቃሉ ብለዋል።
እስራኤልና ሃማስ 47 ሺህ የሚጠጉ ፍልስጤማውያንን ህይወት የቀጠፈውን ጦርነት ለማስቆም ተግባራዊ ማድረግ የጀመሩት ተኩስ አቁም ዛሬ ሶስተኛ ቀኑን ይዟል።