ተኩስ አቁሙ ተግባራዊ በሆነበት የመጀሪያው ቀን ሀማስ 3 ታጋቾችን ሲለቅ፣ እስራኤል ደግሞ 90 ፍልስጤማውያን ለቀቀች
ሀማስ እንደገለጸው ከሆነ ከተለቀቁት እስረኞች መካከል 69 ሴቶችና 21 ታዳጊዎች ይገኙበታል
በቴልአቪቭ ደግሞ 3ቱ ታጋቾች ሲለቀቁ የሚያሳይ ምስል ከጋዛ ቀጥታ ሲተላለፍ በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰዎች በእስራኤል መከላከያ ሚኒስቴር ደጃፍ ደስታቸውን ሲገልጹ ታይተዋል
መካከለኛው ምስራቅን ያመሰው ለ15 ወራት የዘለቀውን ጦርነት ያስቆመው የጋዛ ተኩስ አቁም ተግባራዊ በሆነት በመጀመሪያው ቀን ሀማስ 3 ታጋቾችን የለቀቀ ሲሆን እስራኤል ደግሞ 9ዐ ፍልስጤማውያን እስረኞቸን ለቃለች።
ተኩስ አቁም ፍልስጤማውን በእስራኤል ወደተደበደቡት መንደሮች በመመለስ ህይወታቸውን እንዲጀምሩ፣ የእርዳታ መኪኖች አስፈላጊውን እርዳታ እንዲያደርሱ የሚፈቅድ ነው። በሌሎች የጋዛ አካባቢዎች ነዋሪዎች ከተደበቁበት የሚወጡትን የሀማስ ታጣቂዎች ሰላም ሲሏቸው ተስተውለዋል።
ከእስራኤል እስርቤት የተለቀቁት ፍልስጤማውያን እስረኞች ያሳፈረው ባስ በዌስትባንክ ራማላህ ሲገባ በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች አቀባበል አድርገዋል። ሀማስ እንደገለጸው ከሆነ ከተለቀቁት እስረኞች መካከል 69 ሴቶችና 21 ታዳጊዎች ይገኙበታል።
በቴልአቪቭ ደግሞ 3ቱ ታጋቾች ሲለቀቁ የሚያሳይ ምስል ከጋዛ ቀጥታ ሲተላለፍ በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰዎች በእስራኤል መከላከያ ሚኒስቴር ደጃፍ ደስታቸውን ሲገልጹ ታይተዋል።
የእስራኤል ጦር እንደገለጸው ሮሚ ጎነኒ፣ዶሮን ስቴንብሬቸርና ኢምሊ ደማሪ ከቤተሰቦቻቸው ጋር መቀላቀላቸውንና በጥሩ የጤና ሁኔታ ላይ እንደማገኙ በቪዲዮ አሳይቷል።
"ለሮሚ፣ ዶሮን፣ ኢምሊ ልነግራችሁ የምወደው ሀገሩ ሙሉ ሊያቅፋችሁ ይፈልጋል። እንኳን ደህና መጣችሁ" ሲሉ የእስራኤሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያማን ኔታንያሁ ተናግረዋል። ሴቶቹ በሼባ ሜዲካል ሴንተር ከቤተሰቦቻቸው ጋር ሲገናኙ ለመረጅም ጊዜ ሲተቃቀፉ፣ ሲያለቅሱና ሲስቁ ታይተዋል።
የተለቀቁት ታጋቾች፣ ሀማስ ጥቅምት 7፣2023 ድንበር በመጣስ በደቡብ እስራኤል ጥቃት ፈጽሞ ካገታቸው 250 ሰዎች መካከል ናቸው።
ሀማስ በእስራኤል ላይ የፈጸመውን ጥቃት ተከትሎ እስራኤል በጋዛ በከፈተችው መጠነሰፊ ጥቃት ከ47 ሺ ፍልስጤማውያን መገደላቸውን የጋዛ ጤና ሚኒስትር መረጃ ያመለክታል። በተኩስ አቁም የመጀመሪያ ዙር ትግበራ መሰረት 33 ታጋቾችን በ2000 ገደማ ፍልስጤማውያን የመለወጥ ስራ እንደሚከናወን ተገልጿል።