በ15 ወራት ጦርነት የወደመውን ጋዛ ወደ ነበረበት ለመመለስ 15 አመታትን እንደሚወስድ ተነገረ
ከ2 ሚሊየን በላይ ሰዎች ይኖሩበት የነበረውን ሰርጥ መልሶ ለመገንባት 1.2 ቢሊየን ዶላር ያስፈልጋል ተብሏል
የአደጋ ጊዜ ሰራተኞች በፍርስራሾች ውስጥ የተቀበሩ ሰዎችን የማፈላለግ ስራ ጀምረዋል
መካከለኛው ምስራቅን ወደ ለየለት ሁሉን አቀፍ ጦርነት ሊያስገባ ተቀርቦ የነበረው የሀማስ እና እስራኤል ጦርነት ከ15 ወራት በኋላ በተኩስ አቁም ስምምነት ተቋጭቷል፡፡
የጋዛ ሰርጥን ወደ ፍርስራሽነት የቀየረው እና ከ47 ሺህ በላይ ፍልስጤማውን ንጹሀንን ህይወት የነጠቀው ጦርነት በአለም ላይ ከአስርተ አመታት ወዲህ ከፍተኛ የሰብአዊ ቀውስ ካስከተሉ ጦርነቶች መካከል አንዱ ነው፡፡
በኳታር የተደረሰውን የተኩስ አቁም ስምምነት ተከትሎ በትላንትናው ዕለት በሀማስ እጅ ከሚገኙ 98 ታጋቾች መካከል ሶስቱ ሲለቀቁ እስራኤል በበኩሏ 90 ፍልስጤማውያንን ከእስር በመፍታት የተኩስ አቁሙ ተግባራዊ መደረግ ጀምሯል፡፡
በአሁኑ ወቅት የጦርነቱን መቆም ተከትሎ የጋዛ ባለስልጣናት መልሶ ግንባታ እና አድራሻቸው የጠፉ ሰዎችን ማፈላለግ ላይ ትኩረታቸውን አድርገዋል፡፡
የፍልስጤም የአደጋ ጊዜ አገልግሎት ቃል አቀባይ ማህሙድ ባሳል “ቁጥራቸው 2840 የሚሆኑ አስክሬኖች ለመሰብሰብ በሚያስቸግር ሁኔታ ቀልጠዋል፤ ነገር ግን በፍርስራሾች ውስጥ ተቀብረው የሚገኙ በ10 ሺዎች የሚቆጠሩ ሰማዕታትን ማፈላለግ ጀምረናል” ብለዋል፡፡
በቅርቡ የወጣ አንድ ጥናት በጋዛ የሟቾች ቁጥር ከተጠቀሰው በላይ ሊሆን እንደሚችል፤ በፍርስራሾች ውስጥ የተቀበሩ እና ደብዛቸው የጠፉ ሰዎች አሁን ከተገለጸው የሟቾች ቁጥር ጋር ሲደመር ከ60 ሺህ ሊሻገር እንደሚችል ማመላከቱ ይታወሳል፡፡
በዚህ ወር የወጣው የተባበሩት መንግስታት የጉዳት ግምገማ እንደሚያሳየው በእስራኤል የቦምብ ጥቃት የተከመረውን ከ50 ሚሊዮን ቶን በላይ የሚመዝን ፍርስራሽ ለማጽዳት 21 አመታትን ሊወስድ እንደሚችል ገልጿል፡፡
በተመሳሳይ ባለፈው አመት መጨረሻ ላይ ተመድ ይፋ ያደረገው ሌላ ሪፖር በጦርነቱ የፈራረሱ የጋዛ ሰርጥ መሰረተ ልማቶች ፣ ህንጻ እና መኖሪያ ቤቶችን መልሶ ለመገንባት 1.2 ቢሊዮን ዶላር ወጪ እንደሚፈጅ ጠቅሶ ግንባታው እስከ 2040 ወይም 15 አመታትን ሊወስድ ይችላል ነው ያለው።
የፍልስጤም የአደጋ ጊዜ አገልግሎት የተመድ የጉዳት ግምገማ ሪፖርት የወጣው ባለፈው የፈረንጆቹ አመት መጨረሻ ላይ መሆኑን በመጥቀስ አዲስ የጉዳት ግምገማ ቢከናወን የኪሳራ መጠኑ ከዚህ ሊበልጥ እንደሚችል ገልጿል፡፡
ሮይተርስ በዘገባው ጋዛን መልሶ ለመገንባት የመካከለኛው ምስራቅ ሀገራት እና ሌሎች አጋሮች ድጋፍ ለማድረግ ቃል መግባታቸውን አስታውሷል፡፡
እስራኤል በጦርነቱ በጋዛ የፈጸመችው መጠነሰፊ የአየር ጥቃት ሃማስን ማጥፋት እና ቡድኑ ከመሬት በታች የገነባችውን የዋሻ መሰረተ ልማቶች ማውደም ዋነኛ አላማው እንደነበር ትናግራለች።
ይሁን እና ጥቃቶቹ በትምህርት ቤቶች ፣ ሆስፒታሎች በመንግስት ተቋማት እና በሌሎችም መሰረተ ልማቶች ላይ ከፍተኛ ጉዳት ማድረሳቸው ተመላክቷል፡፡