ሶማሊያ ለዓለም መሳቂያ አድርጎኛል ያለችውን የአትሌቲክስ ሀላፊ ከስራ አገደች
ናስራ አቡካር የተባለች እንስት በቻይና ቼንግዱ የተካሄደውን የ100 ሜትር ውድድር ለማጠናቀቅ 22 ሰከንድ ፈጅቶባታል
የሶማሊያ አትሌቲክስ ፌደሬሽን ሃላፊው ስልጠና ያልወሰደች እንስትን ወደ ቻይና እንድትጓዝ አድርጓል ተብሏል
ሶማሊያ ለዓለም መሳቂያ አድርጎኛል ያለችውን የስፖርት ሚኒስትር ከስራ አገደች፡፡
የቻይናዋ ቼንግዱ የዓለም ዩንቨርሲቲዎች ውድድርን በማስተናገድ ላይ ትገኛለች፡፡
በዚህ ውድድር ላይ በርካታ ዩንቨርሲቲዎች ተማሪዎቻቸውን ልከው በመወዳደር ላይ ሲሆኑ በ100 ሜትር የሴቶች ውድድር ላይ የተፈጠረው ነገር በማህበራዊ ትስስር ገጾች ላይ በስፋት ተሰራጭቷል፡፡
ከጎረቤት ሀገር ሶማሊያ ዩንቨርሲቲዎች ወደ ቻይናዋ ቼንግዱ የተላከችው የ100 ሜትር ተወዳዳሪ የ100 ሜትር ውድድሩን ያጠናቀቀችበት ሰዓት ብዙዎችን አስገርሟል፡፡
ናስራ አቡካር የተሰኘችው የ20 ዓመት ሶማሊያዊት ተወዳዳሪ አንደኛ ከወጣችው ብራዚሊያዊት ጋብርኤላ ማውራኦ 10 ሰከንድ ዘግይታ መጨረሷ ሶማሊያዊያንን አስቆጥቷል፡፡
ተወዳዳሪዋ በውድድሩ ላይ ያሳየችው ፍጥነት ከስፖርተኛ የማይጠበቅ ነው፤ መሳተፍ አልነበረባትም የሚል ትችትም ተበራክቷል።
የውድድሩ ተንቀሳቃሽ ምስልም በብዛት የተሰራጨ ሲሆን ተወዳዳሪዋ በቂ ልምምድ ያልሰራች፣ እውነተኛ አትሌት ያልሆነች እና በዘመድ የተላከች ነች የሚሉ አስተያየቶችም ተንጸባርቀዋል፡፡
የሶማሊያ ዩንቨርሲቲዎች ህብረት በበኩሉ ተወዳዳሪዋ ወደ ቻይና የሀገሪቱን ዩንቨርሲቲዎች ወክላ እንድትወዳደር እንዳልመረጣት እና ማን እንደላካት እንደማያውቅ ነው ያስታወቀው።
የሶማሊያ ስፖርት ሚኒስትር መሀመድ ባሬ በበኩላቸው ተወዳዳሪዋ በቂ ልምምድ አለመስራቷንና አትሌት አለመሆኗን ገልጸው ከዚህ ውርደት ጀርባ ባለው ሰው ላይ እርምጃ እንወስዳለን ሲሉ በወቅቱ በትዊተር ገጻቸው ላይ ጽፈዋል፡፡
የሀገሪቱ ስፖርት ሚኒስቴር ባደረገው ማጣራትም የሶማሊያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ሊቀመንበር ካዲጆ አደን ተወዳዳሪዋን በዝምድና እና በትውውቅ ወደ ቻይና እንደላኳት አረጋግጫለሁ ብሏል፡፡
የሀገሪቱ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ሊቀመንበር ባደረጉት ድርጊትም ከስራቸው መታገዳቸው ተገልጿል፡፡