በአርባምንጭ ከተማ በልመና የሚተዳደሩ ግለሰብ ብዙ ገንዘብ ይዘው መገኘታቸውን ፖሊስ ገለጸ
በአርባምንጭ ከተማ በልመና የሚተዳደሩ ግለሰብ ብዙ ገንዘብ ይዘው መገኘታቸውን ፖሊስ ገለጸ
በአርባ ምንጭ ከተማ ጉርባ ቀበሌ ቅ/ሚካኤል ቤተክርስቲያን አጠገብ በልመና የሚተዳደሩ አንድ ግለሰብ መጠኑ ያልታወቀ ገንዘብ በብዙ ማዳበርያ ይዘው መገኘታቸውን ፖሊስ አስታውቋል፡፡
በልመና የሚተዳደሩት ግለሰብ በቤተክርስቲያኑ አከባቢ ተጠልለው የሚኖሩ ሲሆን የጽዳጽ ባለሙያዎች አከባቢውን ለማጽዳት በተንቀሳቀሱበት ወቅት ነው መጠኑ ያልታወቀው ገንዘብ ሊገኝ የቻለው፡፡
የጽዳት ባለሙያዎቹ ባደረጉት ጥቆማ ፖሊስ ቦታው ድረስ በማቅናት በብዙ ማዳበርያ የታሰሩ የብር ኖቶችን እና ሳንቲሞችን ማግኘቱን አስታውቋል፡፡ አብዛኛው ገንዘብም በአግባቡ ባለመቀመጡ መበላሸቱ ተገልጿል፡፡
የከተማው ፖሊስ አዛዥ ኮማንደር ዳንኤል አረጋ እንደገለጹት ገንዘቡ ተቆጥሮ ከተለየ በኋላ በግለሰቡ ስም አካውንት ተከፍቶ ባንክ ይቀመጣል፡፡
በልመና የሚተዳደሩም ሆነ ማናቸውም የከተማዋ ነዋሪዎች ገንዘባቸውን ደህንነቱ በተጠበቀ መልኩ በባንክ የማስቀመጥ ልምድን የሁልጊዜ ባህላቸው ሊያደርጉ እንደሚገባም ኮማንደሩ መልእክት አስተላልፈዋል፡፡
ከግንዛቤ እጥረት የተነሳ በተመሳሳይ መልኩ ገንዘብን ጥንቃቄ በጎደለው ሁኔታ የሚያስቀምጡ ስለማይጠፉ ባንኮች በከተማዋ ለሚገኙ የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች ግንዛቤ በመፍጠር የሃገርንም ሆነ የግለሰቦችን ሃብት ከብክነት ሊታደጉ እንደሚገባም የፖሊስ አዛዡ አሳስበዋል፡፡
ዘገባው የከተማው ሚዲያና ኮሚዩኒኬሽን ፅ/ቤት ነው፡፡