የጋሞ አባቶችን የሰላም ተምሳሌትነትን የሚዘክር የባህል ሲምፖዚየም በሚሌኒየም አዳራሽ ተካሄደ
የጋሞ አባቶችን የሰላም ተምሳሌትነትን የሚዘክር የባህል ሲምፖዚየም በሚሌኒየም አዳራሽ ተካሄደ
ከዓመት በፊት በአርባ ምንጭ ከተማ ለበቀል ወጥተው የነበሩ ወጣቶችን፣ እርጥብ ሳር በመያዝ በቆየ ባህላዊ ልምዳቸው ከበቀል እርምጃቸው እንዲቆጠቡ ያደረጉ የጋሞ አባቶች ከፍተኛ ክብር እና ከፍተኛ አድናቆት አትርፈዋል፡፡
ይህ በሌሎች ሀገራትም ጭምር እውቅናን ያገኘው የጋሞ አባቶች ዘመን ተሻጋሪ ባህላዊ የግጭት አፈታት ጥበብ በተለያየ መልኩ ሲዘከር ቆይቷል፡፡
የጋሞ ልማት ማህበር አዲስ አበባ ቅርንጫፍ ደግሞ የጋሞ አባቶች ተግባር እና የብሄሩ ባህል የሚዘከርበትን የማጠቃለያ ሲምፖዚየም በሚሌኒየም አዳራሽ አዘጋጅቷል፡፡
በአዲስ አበባ ለመጀመሪያ ጊዜ በተዘጋጀው በዚህ ሲምፖዚየም ላይ ከፍተኛ ባለስልጣናትን ጨምሮ ከ20 ሺ በላይ የጋሞ ተወላጆች እና ወዳጆች ተሳትፈዋል፡፡
ጋሞ በእውነተኛ የፍቅር እና የአንድነት ስሜት እንዲሁም በተግባራዊ አቃፊነት ያሳየውን ጠንካራ የሰላም ወዳድነት ተግባር አጠናክሮ እንዲቀጥል መልእክት ያስተላለፉት የጋሞ ዞን አስተዳዳሪ አቶ ብርሀኑ ዘውዴ፣ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ለብሄሩ ባህል ማእከል ግንባታ የሚሆን ቦታ እንዲሰጥ ጥያቄ አቅርበዋል፡፡
“የጋሞ ህዝብ ትልቅ ነው ስንል እንዲሁ ለፖለቲካ ፍጆታ ሳይሆን ትልቅነትን በመንበርከክ ውስጥ በተግባር በማሳየቱ ነው” በማለት የጋሞ አባቶችን ተምሳሌታዊ ተግባር ያደነቁት የአዲስ አበባ ከተማ ም/ ከንቲባ ኢንጅነር ታከለ ኡማ ለጋሞ ባህል ማእከል ግንባታ ቦታ በአስተዳደሩ እንደሚዘጋጅ ቃል ገብተዋል፡፡ የብሄሩን ባህል፣ ጥበብ እና እሴት ለትውልድ ለማስተላለፍ ይረዳል የተባለውን የባህል ማእከል አስተዳደሩ ከብሄሩ ባለሀብቶች እና ከህብረተሰቡ ጋር በመተባበር እንደሚገነባም ኢንጅነር ታከለ ቃል ገብተዋል፡፡
የሰላም ሚኒስትር ወይዘሮ ሙፊሪያት ካሚል ባደረጉት ንግግር ደግሞ የሰላም ጉዳይ የመንግስት ብቻ አለመሆኑን በመረዳት የጋሞ አባቶች በባህላዊ መንገድ ሰላምን ለማረጋገጥ ያከናወኑት ተግባር አርአያ መሆኑን በመግለጽ ተጨማሪ ጥናቶች ተደርገውበት ለሌላውም ዓለም ተምሳሌት የሚሆን ኢትዮጵያዊ እሴትነቱ ሊጎላ እንደሚገባ ተናግረዋል፡፡
የአባቶች ባህላዊ እሴት እንዳለ ሆኖ፣ ወጣቶች ባህሉን ሳይዘነጉ የአባቶቻቸውን ምክር በመስማታቸው የሰላም ሚኒስትሯ ለጋሞ ወጣቶች የተለየ ምስጋና አቅርበዋል፡፡
የጋሞ አባቶችን ባህላዊ እሴት በተመለከተ አል-ዐይን ያናገራቸው ከብሄሩ አባቶች መካከል አንዱ የሆኑት ሰዲቃ ስሜ ባህሉ ተጠብቆ እስካሁን የቆየው ህብረተሰባዊ መሰረት ስላለው ነው ብለዋል፡፡
“የጋሞ ወላጆች ልጆቻቸውን ህብረተሰቡ በባህሉ እንዲያሳድግ ያደርጋሉ እንጂ እያንዳንዱ ቤተሰብ ለራሱ ልጆች ብቻ አይጨነቅም” ሲሉ ገልጸዋል፡፡
ልጆችን በመልካም ባህል እና ስነ ምግባር ማነጽ የምንችለው እኛ አባቶች ነን የሚሉት አቶ ሰዲቃ ስሜ በሁሉም የኢትዮጵያ አካባቢዎች መሰል ተግባራት ትኩረት ሊሰጥባቸው ይገባል ብለዋል፡፡
በአዳራሹ በነበረው ዝግጅትም ወጣቶች የነበራቸው ስሜት እና ለታላላቆቻቸው የሚያሳዩት አክብሮት የኋላ ማንነታቸውን እና አስተዳደጋቸውን የሚያንጸባርቅ እንደሆነ ታዝበናል፡፡
ከታዳሚያኑ አንዱ የሆነው ወጣት መልስ ጎዴቦ ዘመናትን በተሸገረው የብሄሩ አባቶችን የመስማት ባህል ኩራት እንደሚሰማው ነግሮናል፡፡
ወጣቱ ከአል-ዐይን ጋር በነበረው ቆይታ ይህ ባህል እርሱም ያደገበት መሆኑን እና አሁን ደግሞ ባህሉ ይበልጥ ጎልቶ እውቅና ማግኘቱ ይበልጥ የሚያበረታታ ነው ብሏል፡፡
በሌሎች የኢትዮጵያ ብሄሮች እና ብሄረሰቦች ዘንድም መሰል አኩሪ ባህሎች አሉ የሚለው መልስ እነዚህን ባህሎች ተግባራዊ በማድረግ መላው የኢትዮጵያ ወጣቶች ሰላምን ከማረጋገጥም ባለፈ መልካም ስነምግባርን ለቀጣዩ ትውልድ ሊያስተላልፉ ይገባል ሲልም ሀሳቡን ሰንዝሯል፡፡
በዝግጅቱ ላይ የተለያዩ ጋሞን የሚያንጸባርቁ ባህላዊ ክዋኔዎች የቀረቡ ሲሆን ከፍተኛ የመንግስት ባለስልጣናት የጋሞ አባቶችን ተምሳሌትነት በማንተባረቅ እርጥብ ሳር ይዘው በመንበርከክ ወጣቱ ሰላሙን እንዲጠብቅ ተማጽነዋል፡፡