“…በጥይት…የተመታሁት ጀርባዬን ከሆነ ስሸሽ ነው[ስጋየን] አሞራ ይብላው…” -ፊታውራሪ ገበየሁ
“…በጥይት…የተመታሁት ጀርባዬን ከሆነ ስሸሽ ነው[ስጋዬን] አሞራ ይብላው…” -ፊታውራሪ ገበየሁ
የአድዋ ጦርነት በ1888ዓ.ም በኢትዮጵያውያንና ጣሊያን መካከል የተካሄደ ጦርነት ሲሆን በጦርነቱ ኢትዮጵያውያን ድል አድርገዋል፡፡
በወቅቱ ዳግማዊ አጼ ሚኒልክ የውጭ ጠላት የኢትዮጵያን የባህር በር አልፎ መምጣቱን በአዋጅ በማስነገር ህዝቡ እንዲሰማ አደረጉ፤ ህዝቡም በአድዋ ዘመቻ ተከተላቸው፡፡
ጥሪውን ተቀብለው ከዘመቱ አርበኞች መካከል የጦር አበጋዝ የነበሩት ፊታውራሪ ገበየሁ ግንባር ቀደም መሆናቸው ይነገርላቸዋል፡፡
የጦር ጀነራሉ ፊታውራሪ ገበየሁ በቀድሞው አጠራር ሸዋ ግዛት በአንጎለላ ነው የተወለዱት።
ፊታውራሪ ገበየሁ ለአድዋ ጦርነት ከውጊያ በዘለለ የወገን ጦር ወኔ እንዲኖረው በማድረግ በኩል ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንደነበራቸውም ይወሳል።
እርሳቸውም "በጦርነት ስዋጋ በጥይት ተመትቼ ብወድቅ የተመታሁት ጀርባዬን ከሆነ ስሸሽ ነው አሞራ ይብላው እዛው ተውኝ ፤ ግንባሬን ከተመታሁ ግን ሃገሬ ቅበሩኝ" ብለው መናገራቸውን ታሪክ መዝግቦታል።
ፊታውራሪ ገበየሁ በአድዋ ጦርነት የተሰው ሲሆን አጽማቸውም በተናዘዙት መሰረት አንጎለላ ኪዳነ ምህረት ቤተ ክርስቲያን በሳጥን ውስጥ በመስታወት ፍሬም ተቀምጦ ይገኛል።
የፊታዉራሪ ገበየሁን መሞት የሰሙት የኢትዮጵያ ንጉሰ ነገስት ዳግማዊ አጼ ሚኒልክ ሀገሬን አዳንኩ ገበየሁንም አጣሁ ማለታቸውን እንዲሁ ታሪክ ጽፎታል።
በጦርነቱ ወቅት የኢትዮጵያ የጦር አበጋዝ ፊታውራሪ ገበየሁ መሞታቸው ሲሰማ፣ "ገበየሁ ቢሞት ተተካ ባልቻ መድፍ አገላባጭ ብቻ ለብቻ" በሚል ግጥም ተገጥሞላቸዋል።
የአድዋ ድል የኢትዮያውያን ብቻ ሳይሆን የመላው ጥቁር ህዝብ ድል ተብሎ በታሪክ ተመዝግቧል፡፡ የጣሊያንን ጦር መሸነፍ በሰሙ ጊዜ ጣሊያናውያን አደባባይ ወጥተው የሀገራቸውን መንግስት ተቃወሙ፤ “ቪቫ ጣይቱ፤ ቪቫ ምኒሊክ” በማለት የስላቅ መልእክትም አስተላልፈው ነበር፡፡