ገደቢስ በተባለው አውሮፕላን አደጋ ምክንያት ህይወታቸውን ያጡ ሰዎች ተዘክረዋል
ገደቢስ በተባለው አውሮፕላን አደጋ ምክንያት ህይወታቸውን ያጡ ሰዎች ተዘክረዋል
ወ/ሮ ፋንታዬ ደሳለኝ የኢትዮጵያ አየር መንገድ የሆነው ቦይንግ 737 ማክስ 8 አውሮፕላን ወድቖ ሲከሰከስ በቦታው የነበሩ የአይን እማኝ ናቸው፡፡
ገደቢስ በተባለው አደጋ ህይወታቸውን ያጡ ሰዎች እስካሁን ከአይነ ህሊናቸው እንዳልጠፋ የሚናገሩት ወ/ሮ ፋንታዬ አደጋው በተከሰተበት ቦታ በኢጄሬ “ሙትአመት” ሲዘክሩ አግኝተናቸዋል፡፡
አደጋው ሲታወስ
ከአንድ ዓመት በፊት የዓለም ህዝብን ያስደነገጠና የአውሮፕላን አደጋ በአዲስ አበባ አቅራቢያ ተከስቶ ነበር፡፡ይህ በአቪየሽን ዘርፍ ትልቅ ሃዘንን የፈጠረ አጋጣሚ የ 157 ሰዎችን ህይወት አሳጥቷል፡፡ አደጋው የደረሰው ከአዲስ አበባ ተነስቶ ወደ ናይሮቢ እየበረረ በነበረ አውሮፕላን ላይ ነው፡፡
የበረራ ቁጥር ኢቲ 302 የሆነና ንብረትነቱ የኢትዮጵያ አየር መንገድ የሆነው ቦይንግ 737 ማክስ 8 አውሮፕላን በኦሮሚያ ክልል ምስራቅ ሸዋ ዞን የጊምቢቹ ወረዳ ነበር የተከሰከሰው፡፡
በወቅቱ የአካባቢው ነዋሪዎች በአቅራቢያቸው ከፍተኛ ጭስ መመልከታቸውን ይናገራሉ፡፡ከዛም ወደ ስፍራው ሲያመሩ የሆነው ሁሉ አስደንጋጭና አሳዛኝ ነበር፡፡ ዓለምን በእጅጉ ያሳዘነውን ሀዘንም ዓመቱን ሙሉ እያስታወሱ መቆየታቸውን ተናግረዋል፡፡
አደጋው ከደረሰበት ጊዜ አንስቶም በአካባቢው ባህል መሰረት መታሰቢያ ሲደረግ የቆዩ ሲሆን በኢትጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ የእምነት ሥርዓት ሰባት፣ 12፣ 42፣መንፈቅና ዓመትን አስበው ቁርባን አስቆርበዋል፡፡
ይህ የአካባቢው ነዋሪዎች ድንበር ተሸጋሪ ደግነት በበርካቶች እየተደነቀ ነው፡፡
የቱሉ ፈራ እና ሃማ ቁንጥሽሌ ቀበሌዎች
የአውሮፕላን አደጋው በነዚህ ቀበሌዎች አዋሳኝ የደረሰ ሲሆን ቀድመው የደረሱትም እነዚህ የአካባቢው ነዋሪዎች ናቸው፡፡ ወ/ሮ ፋንታዬ ደሳለኝ የአካባቢው ነዋሪ ሲሆኑ ባለፈው ዓመት አውሮፕላኑ ሲከሰከስ በቅርብ ርቀት ላይ ነበሩ፡፡ እርሳቸው እንደሚሉት አውሮፕላኑ ሊወድቅ ሲል ከፍተኛ ጭስ ነበረ በወቅቱም እርሳቸው ውሃ እየቀዱ እንደነበር ግልጸዋል፡፡ ውሃ መቅዳታቸውን አቋርጠው በፍጥነት አውሮፕላኑ ወደ ወደቀበት ቦታ ማምራታቸውን የሚናገሩት ወ/ሮ ፋንታዬ በቦታው እንደደረሱ ከፍተኛ ድንጋጤ ላይ እንደነበሩ አስታውሰዋል፡፡ የአካባቢው ነዋሪዎችም ከያሉበት ተሰባስበው ሃዘናቸውን መግለጽ መጀመራቸውን አስታውሰዋል፡፡
የኢጄሬ ከተማ ነዋሪዎቹ ወ/ሮ እመቤት አለማየሁ እና ወ/ሮ አየለች ሙሉጌታ አደጋው እንደተከሰተ የኢትዮጰያ አየር መንገድ መኪኖች በፍጥነት ሲመላለሱ ምን እንደተከሰተ መጠየቃቸውን አስታውሰዋል፡፡ ችግር መከሰቱን ከሰሙ በኋላም አደጋው ወደ ደረሰበት ቦታ የሚሄዱ ሰዎችን መንገድ በማሳየት፣አስፈላጊ ደጋፍ በማድረግ ትብብር ሲያደርጉ እንደነበር ተናግረዋል፡፡
እነዚሁ ነዎሪዎችም አደጋው ከደረሰ ጊዜ አንስቶ በተለያየ መንገድ ሀዘናቸውን ሲገልፁ ቆይተዋል::
በኢትዮጵያ ኦርቶዶክ ተዋህዶ ዕምነት መሰረትም ወቅቱን እየጠበቁ የሙት መታሰቢያ ያደረጉ ሲሆን በትናንትናው ዕለትም የሙት ዓመት መታሰቢያ አካሂደዋል::