ለጥቃቱ እስካሁን ሃላፊነቱን የወሰደ የለም
በሰሜናዊ አፍጋኒስታን የተፈጸመ የቦምብ ጥቃቱ በጥቂቱ የ10 ተማሪዎችን ህክይወት መቅጠፉ ተነገረ።
ሀገሪቱን እየመራ ያለው ታሊባን እንዳስታወቀው የቦምብ ፍንዳታው በሳማንጋን ግዛት አይባክ በተሰኘችው ከተማ የሚገኝ ሃይማኖታዊ ትምህርት ቤትን ኢላማ ያደረገ ነው።
ተማሪዎች እና ንጹሃን ላይ ያነጣጠረው ጥቃት በርካቶችን ማቁሰሉን የአፍጋኒስታን የሀገር ውስጥ ጉዳዮች ሚኒስቴር ገልጿል።
የሟቾቹ ቁጥርም ከተጠቀሰው ከፍ እንደሚል የአካባቢው ሆስፒታል መግለጹን አጃንስ ፍራንስ ፕሬስ ዘግቧል።
ተማሪዎቹ ከጸሎት ሲመለሱ የፈነዳው ቦምብ ከተማሪዎቹ ባሻገር ሌሎች ንጹሃንን ማቁሰሉ ተነግሯል።
ለጥቃቱ እስካሁን ሃላፊነቱን የወስደ አካል የለም።
የአፍጋኒስታን የሀገር ውስጥ ጉዳዮች ሚኒስቴር ቃል አቀባዩ አብዱል ናፊ ታኩር፥ የታሊባን የጸጥታ ሃይሎች ለዚህ ጥቃት ማን እጁ እንዳለበት እያጣሩ ነው ብለዋል።
የማጣራት ስራው ሲጠናቀቅም ጥቃት አድራሾቹ ተገቢውን ዋጋ ያገኛሉ ሲሉ ዝተዋል።
አፍጋኒስታን ታሊባን ስልጣን ከመያዙ በፊትም ሆነ በኋላ የቦምብ ጥቃት በተደጋጋሚ ይፈጸምባታል።
ባለፈው ወር በመዲናዋ ካቡል በሚገኝ ትምህርት ቤት ላይ በተፈጸመ ጥቃት 52 ተማሪዎች መገደላቸው የሚታወስ ነው።
ታሊባን በነሃሴ ወር 2021 ዳግም ወደ ስልጣኑ ከተመለሰ በኋላ ለተፈጸሙ የሽብር ጥቃቶች አይ ኤስ በተደጋጋሚ ሃላፊነት ሲወስድ ይታያል።