የአሜሪካና የታሊባን አመራሮች ለመጀመሪያ ጊዜ ፊት ለፊት ተገናኝተው ተወያዩ
ውይይቱ በጋራ ጉዳዮች ከመምከር ባለፈ ለታሊባን ሕጋዊ ዕውቅና መስጠት እንዳሆነ አሜሪካ ገልጻለች
በውይይቱ የአፍጋኑ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር “ማንም በማንም ሀገር የውስጥ ፖሊሲዎች ጣልቃ እንዳይገባ” አስጠንቅቀዋል
አሜሪካ ወታደሮቿን ከአፍጋኒስታን ካስወጣች በኋላ የአሜሪካ አመራሮች ለመጀመሪያ ጊዜ ከአፍጋኒስታን አመራሮች ጋር ፊት ለፊት ተገናኝተው ውይይት ማድረጋቻ ተገለፀ።
በኳታር ዶሃ የተደረገው ውይይት ዋነኛ አንኳር ሃሳቦች አክራሪ ቡድኖችን መቆጣጠር፣ የአሜሪካ ዜጎችን ሰላማዊ በሆነ መንገድ ከአፍጋኒስታን ማስወጣት እና ሰብዓዊ ዕርዳታን የተመለከተ እንደነበርም ሲ.ቢ.ኤስ ኒውስ የአሜሪካ ባለስልጣናትን ዋቢ አድርጎ ዘግቧል።
የአፍጋኒስታኑ ታሊባን የሾመው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አሚር ካን ሙታኪ ከአሜሪካ ጋር ያደረጉት ውይይትን አስመልክቶም ሁለቱ ወገኖች በ2020 የተፈረመውን የዶሃ ስምምነት ውል ለማክበር መስማማታቸውን ተናግረዋል።
የዶሃው ስምምነት እንደ አልቃይዳ ያሉ ቡድኖች በአሜሪካ እና የአጋሮቿን ደህንነት አደጋ ላይ እንዳይጥሉ እርምጃዎችን ለመውሰድ ሰፊ ግዴታዎችን በታሊባን ላይ ጥሏል።
የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ የአሜሪካ ባለስልጣናት ለታሊባን የኮቪድ ክትባቶችን እና የሰብአዊ ዕርዳታን ለማድረስ ድጋፍ እንዲያደርጉ ከስምምነት መደረሱም ተናግሯል።
አሜሪካ በቅዳሜው ውይይቶች ዙሪያ ዝርዝር ጉዳዮች ላይ እስካሁን አስተያየት አልሰጠችም።
ሆኖም ግን የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ቀደም ሲል፤ ታሊባን የሴቶችን መብት እንዲያከብር ፣ ሁሉን ያካተተ መንግሥት እንዲመሰረት እና የሰብዓዊ ድርጅቶች እንዲሠሩ ለመፍቀድ ውይይቱን እንደሚጠቀሙበት ማናገራቸው ይታወሳል።
ስብሰባው በዛሬው ዕለት እሁድ እንደሚቀጥል ተገልጿል።
የአፍጋኑ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ለጋዜጠኞች እንደገለፁት “ታሊባን ከዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ጋር ያለውን ግንኙነት ማሻሻል ይፈልጋል” ያሉ ሲሆን፤ “ማንም በማንም ሀገር የውስጥ ፖሊሲዎች ውስጥ ጣልቃ መግት የለበትም” ሲሉም አስጠንቅቀዋል።
የአሜሪካ ባለሥልጣናት ውይይቱ ከታሊባን ጋር በብሔራዊ ጥቅም ጉዳዮች ላይ መቀጠሉን እንጂ “ለቡድኑ ሕጋዊ ዕውቅና መስጠት አይደለም” ብለዋል።
ውይይቱ የተደረገው አፍጋኒስታን የከፋ የሚባለውን የአጥፍቶ ጠፊ ጥቃት ካስተናገደች ከአንድ ቀን በኋላ ነው።
በሰሜናዊ ኩንዱዝ ከተማ በሚገኝ መስጊድ ላይ በተፈጸመው የአጥፍቶ ጠፊ የቦምብ ጥቃት ቢያንስ 50 ሰዎች ሲሞቱ ከ 100 በላይ ቆስለዋል።
ጥቃቱ የተፈፀመበት የሰይድ አባድ መስጊድ የሺዓ ሙስሊሞች ብበዛት የሚያዘወትሩት ሲሆን የተለያዩ ግዛቶችን የሚያስተዳድረው የእስልምና መንግሥት ቡድን ከጥቃቱ ጀርባ እጁ እንዳለ አስታውቋል።
በአፍጋኒስታን የአርብ ጥቃት ሰለባ ለሆኑ ሰዎች የቀብር ሥነ ሥርዓቶች በመደረግ ላይ ናቸው።
የተባበሩት መንግስታት የሰሞኑን ጥቃት "በዚህ ሳምንት በሃይማኖታዊ ተቋም ላይ ያነጣጠረ ሦስተኛ ገዳይ ጥቃት ነው። ይህ የሚያሰቅቅ የአመፅ ዘይቤ" አካል ነው ብሏል።