የሟቾቹ ቁጥር ሊጨምር እንደሚችል ተገልጿል
በሕንድ ህንጻ ተደርምሶ 13 ሰዎች ሞቱ
በምዕራባዊ ሕንድ አንድ ህንጻ ተደርምሶ 13 ሰዎች ሲሞቱ 25 ደግሞ በተደረመሰው ህንጻ ፍርስራሽ ውስጥ መቅረታቸውን የአካባቢው ባለሥልጣናት አስታወቀ፡፡
የድንገተኛ አደጋ ሰራተኞች የአራትና የሰባት ዓመት ልጆችን ጨምሮ 20 ሰዎችን ማዳናቸውን ሲጂቲኤን ዘግቧል፡፡ አደጋው ከሙምባይ በቅርብ ርቀት በምትገኘው ብሂዋንዲ የደረሰ ሲሆን የሀገሪቱ ብሔራዊ አደጋ ምላሽ ተቋም እንደገለጸው እስካሁን ባለው መረጀ የሟቾች ቁጥር 13 ደረሷል፡፡
የተቋሙ ዳይሬክተር ሳተያ ናራያን ለነፍስ አድን ስራ አነፍናፊ ውሾንና የባለሙያዎች ቡድን አደጋው ወደተከሰተበት አካባቢ ቦታ መላካቸውን የገለጹ ሲሆን 40 የአደጋ ጊዜ ሰራተኞችም መሳተፋቸውን ገልጸዋል፡፡
የአደጋው መንስዔ ምን እንደሆነ እስካሁን ይፋ አልተደረገም ነው የተባል፡፡ ይሁንና በሕንድ ከሰኔ እስከ መስከረም ድረስ የህንጻዎች መደርመስ የተለመደ መሆኑም በዘገባው ተካቷል፡፡