ከዓለም 30 የተበከሉ ከተሞች 21ዱ ህንድ ውስጥ ይገኛሉ
ከዓለም 30 የተበከሉ ከተሞች 21ዱ ህንድ ውስጥ ይገኛሉ
ህንድ አስከፊ የአየር ንብረት ባላቸው ከተሞች ብዛት በድጋሚ በዓለም ቀዳሚውን ስፍራ መያዟን አንድ ሪፖርት ጠቁሟል፡፡ የቻይና ከተሞች በአንጻሩ ካለፈው ዓመት መሻሻል አሳይተዋል ነው የተባለው፡፡
የ2019 የዓለም አየር ደህንነት ሪፖርት እንደሚያመለክተው ከቀዳሚዎቹ 30 የተበከሉ የዓለም ከተሞች 21ዱ የህንድ ከተሞች ናቸው፡፡ ከነዚህም ስድስቱ ከመጀመሪያዎቹ 10 የተበከሉ ከተሞች ዝርዝር ውስጥ ናቸው፡፡
በዋና ከተማዋ ኒው ዴልሂ አቅራቢያ ላይ የሚገኘው ጋዚአባድ ከተማ በየአየር ንጽህና መረጃ ቋት ልኬት 110.2 በማስመዝገብ በዓለማችን ተስተካካይ ያልተገኘለት የተበከለ ከተማ ሆኗል፡፡ ይሄም የአሜሪካ የከባቢ አየር ጥበቃ ኤጀንሲ ለጤናማ አየር ከሚያስቀምጠው ቁጥር ከሁለት እጥፍ በላይ የሚልቅ ነው፡፡
ዴልሂ ደግሞ በአየር ብክለት በዓለም አምስተኛ ደረጃን ይዛለች፡፡
ባለፈው ህዳር ወር የዴልሂ አየር ንጽህና መረጃ ቋት ልኬት በአንዳንድ የከተማዋ አካባቢዎች አደገኛ ከሚባለው መጠን በሶስት እጥፍ ከፍ በማለት ከ800 በልጦ የጤና አስቸኳይ ጊዜ ታውጆ እንደነበር ሲኤንኤን በዘገባው አስታውሷል፡፡
ከቀዳሚዎቹ 30 የተበከለ አየር ያለባቸው ከተሞች 27ቱ በደቡብ ኤሲያ ሀገራት የሚገኙ ናቸው፡፡
በአህጉር ደረጃም ቢሆን ኤሲያ በ2019 በአየር ብክለት መጠን የፊተኛውን ደረጃ ይዛለች፡፡ ባንግላዴሽ፣ ፓኪስታን፣ ሞንጎሊያ፣ አፍጋኒስታንና ህንድን ጨምሮ በአለማችን ጤናማ ያልሆነ አየር ያለባቸው ከአንድ እስከ አስራ ሦስት ያሉ ሀገራት ሁሉም በኤሲያ የሚገኙ ናቸው፡፡
በፓኪስታን ላሆሬ በተበከለ አየር ውስጥ የሚሰራው ጸጉር አስተካካይ
የዓለም ጤና ድርጅት መረጃ እንደሚያሳየው በየዓመቱ 7 ሚሊዮን ህዝብ ከአየር ብክለት ጋር በተያያዘ በሚከሰቱ ህመሞች ህይወቱ ያልፋል፡፡
ምንጭ፡- ሲኤንኤን