500 የልማት ቡድኖች እንቦጩን በማስወገድ ስራ ላይ ተሰማርተዋል
እንቦጭን ከጣና ሐይቅ የማስወገድ ዘመቻ ተጀመረ
በውሃ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስቴርና በአማራ ክልል ፕሬዝዳንት ጽ/ ቤት አስተባባሪነት ለ30 ቀናት የሚቆይ እንቦጭን ከጣና ሐይቅ የማስወገድ ዘመቻ ዛሬ ጥቅምት 9 ቀን 2013 ዓ.ም በተደራጀ መንገድ ተጀምሯል፡፡
በዘመቻው ላይ የውሃ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስትሩ ዶ/ር ኢ/ር ስለሺ በቀለ ፣ የአማራ ክልል ምክትል ርእሰ መስተዳድር ዶ/ር ፋንታ ማንደፍሮ እና ሌሎችም የፌዴራልና የክልሉ ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች ተገኝተዋል።
የውሃ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስትር ዶ/ር ኢ/ር ስለሺ በቀለ
“ህዳሴ ከዓባይ ዓባይ ከጣና አይነጣጠሉም” በሚል መሪ ቃል ፣ ዘመቻው የተጀመረው በጎንደር ዙሪያ ወረዳ ምጥረሃ ቀበሌ ሲሆን እንቦጩ በተስፋፋባቸው ሁሉም የሐይቁ ዙሪያ አካባቢዎች የሚቀጥል ይሆናል፡፡
አል ዐይን አማርኛ ከሚኒስቴሩ ያገኘው መረጃ እንደሚያመለክተው እያንዳንዳቸው 20 አባላት ያሏቸው 500 የልማት ቡድኖች እንቦጩን በማስወገድ ስራ ላይ ተሰማርተዋል፡፡
ለስራው የሚሆን የገቢ ማሰባሰቢያ ስራ እንደሚከናወንም ሚኒስቴሩ ለአል ዐይን ገልጿል፡፡
እንቦጭ የተንሰራፋበት የጣና የውሃ አካል ለሁሉም ክልሎች፤ የከተማ አስተዳደሮች እና የፌደራል እና የክልል ተቋማት እንዲሁም መንግስታዊ ላልሆኑ አካላት ተከፋፍሎ እንደሚሰጥም ነው የተገለጸው፡፡ ከክልሎች እስ ተቋማት ተከፍሎ የተሰጣቸውን በእንቦጭ የተወረረ ቦታ በአንድ ወር ጊዜ ውስጥያስወግዳሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡
ዛሬ የተጀመረው ዘመቻ እስከ ህዳር 9 የሚቆይ ሲሆን በዚህ የጊዜ ገደብ በተባበረ ሃገራዊ አቅም የእንቦጭ አረምን ከጣና ሃይቅ ላይ ለማስወገድ ይሠራል ነው የተባለው፡፡