የጉና ተራራ አካባቢ መራቆት ለእምቦጭ መስፋፋት መልካም አጋጣሚ መፍጠሩ ይታመናል
እምቦጭን ለማጥፋት ዘላቂው መፍትሔ ምንድን ነው?
የጣና ሐይቅ በኢትዮጵያ ከሚገኙ ሃይቆች ትልቁ ሲሆን 84 ኪሎ ሜትር ርዝመትና 66 ኪሎ ሜትር ስፋት አለው፡፡ በአጠቃላይም 3 ሺ 500 ካሬ ኪሎ ሜትር የሚሸፍን ሲሆን ብዙ ደሴቶችም ይገኙበታል፡፡ አንዳንዶቹ በተለይም በዳጋ ደሴት የድሮ የኢትዮጵያ መሪዎች መቃብሮች እንደሚገኙ ተግልጿል፡፡
በኢትዮጵያ ውስጥ ክርስትናን ለመጀመሪያ ጊዜ ያስተዋወቁት አቡነ ሰላማ መቃብርም በዚሁ በጣና ሃይቅ ላይ እንደሚገኝ መረጃዎች ያመለክታሉ። ከሐይቁ መጋቢ ወንዞች መካከል ግልገል ዓባይ፣ መገጭ፣ ርብ እና ጉማራ ሲሆኑ የሐይቁን ዓመታዊ የውሃ ፍሰት 95 በመቶ ይሸፍናሉ፡፡ አሁን ባለው ይዞታ የጣና ሃይቅ በዓመት 1ሺ 454 ቶን አሳ ምርት ይመረታል። ይሁንና አሁን ላይ ሃይቁ በእምቦጭ አረም የመወረር አደጋ አጋጥሞታል፡፡
በርካቶች በዚህ ዙሪያ መነጋገር ከጀመሩ ቢቆዩም ዘላቂው መፍትሄ ላይ ግን መግባባት ሳይደረስ ቆይቷል፡፡ የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ መንግሥት የችግሩን አሳሳቢነት በመረዳት ከአውሮፓ የተሻለ ማሽን ለመግዛትና በሰው ኃይል ታግዞ ለማስወገድ እየተሰራ መሆኑን መግለጻቸው የሚታወስ ሲሆን ይህም ጊዚያዊ መፍትሄ መሆኑን ነው የተናገሩት፡፡
ከወራት በፊት የጣና ሐይቅን በእምቦጭ አረም መወረር በተመለከተ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባል ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ጥያቄ ማቅረባቸው ይታወሳል፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በማብራሪያቸውም እምቦጭን በሰውሃይል እና በማሽን ማስወገድ ጊዜያዊ መፍትሔዎች መሆናቸውን መግለጻቸው ይታወሳል፡፡ ዶ/ር ዐቢይ የተፈጥሮ ሀብት ጥበቃ ሥራን ማጠናከር በዘላቂነት ሃይቁን ለመታደግ እንደሚያግዝ አስታውቀዋል፡፡
የጣና ሐይቅና የተከዜ ወንዝ ተፋሰስ መነሻ የሆነው የጉና ተራራ አካባቢ መራቆት ካልተመለሰ እምቦጭን በዘላቂነት ማስወገድ እንደማይቻልም የጠቀሱት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ከ4 ሺህ ሜትር በላይ ከፍታ ያለው የጉና ተፋሰስን የተፈጥሮ ሀብት መጠበቅና እንደ ርብ እና ጉማራ ያሉ ወንዞች ከፎገራና አካባቢው ወደ ጣና ሐይቅ የሚያስገቡትን የእምቦጩን ምግብ ማስቀረት እንደሚገባም መግለጻቸው ይታወሳል፡፡
በደብረ ታቦር ዩኒቨርሲቲ ጉና ጣና የተቀናጀ የመስክ ምርምርና ልማት ማዕከል ተመራማሪና አስተባባሪ እንዲሁም በተፈጥሮ ሀብት ትምህርት ክፍል መምህር አቶ ኃይሉ ምናለ ጣና ሃይቅን ከእምቦጭ ለመታደግ ዘላቂው መፍትሄ መልሶ ማልማት እንደሆነ ገልጸዋል፡፡
አቶ ኃይሉ ምናለ
ለጣና ሐይቅ ዓመታዊ የውኃ ፍሰት 42 ነጥብ 9 በመቶ የሚሸፍኑት ጉማራና ርብ ወንዞች መነሻቸው የጉና ተራራ ነው፡፡ የውሃ ፍሰት ብቻ ሳይሆን ወደ ሃይቁ የሚገባው 42 ነጥብ 9 በመቶ ደለልም ከነዚህ ወንዞች የሚነሳ እንደሆነ ተመራማሪው ያነሳሉ፡፡
ከጉና እስከ ጣና የተራራውን ሰንሰለት ተከትለው የሚከናወኑ እንቅስቃሴዎች ማለትም የእርሻ ስራ፣ የከተማ ስራዎች፣ የሰዎች እንቅስቃሴዎች እና ሌሎችም በጊዜ ሂደት በአካባቢው አፈር እንዲከላ እንደሚያደርጉም ይገለጻሉ፡፡ በዚህ የአፈር መከላት አካባቢው ከመሸርሸሩም በላይ ለእምቦጭ ምቹ የሚሆኑ ምግቦች አብረው ወደ ጣና ይሄዳሉ ይላሉ አቶ ኃይሉ፡፡ ይህም እምቦጩ እንዲስፋፋ ያደርጋል የሚሉት ተመራማሪው አፈር እንዳይሸረሸር ማድረግ እንደሚገባ ያነሳሉ፡፡ ይህንን ለማስቀረት በጉና ተራራ ላይ ተፈጥሮ እንዳይዛባ አካባቢውን ማልማት ይገባል በማለት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ የጠቀሱት ሃሳብ ትክክል ስለመሆኑም ነው አቶ ኃይሉ የሚገልጹት፡፡
ተመራማሪው አቶ ኃይሉ የተፋሰሱን የተፈጥሮ ሀብት መጠበቅ እንደ ርብ እና ጉማራ ያሉ ወንዞች ከፎገራና አካባቢው ወደ ጣና ሐይቅ የሚያስገቡትን የእምቦጩን ምግብ በማስቀረት እምቦጭን ብቻ ሳይሆን የጣና ሐይቅን የውኃ ጥልቀት ሊቀንስ የሚችል ደለልንም መከላከል እንደሚቻል ያነሳሉ፡፡
ይህንን ለማድረግ ደግሞ የደብረታቦር ዩኒቨርሲቲ ጉና ጣና የተቀናጀ የመስክ ምርምርና ልማት ማዕከል
አቋቁሞ እየሰራ መሆኑንም ነው አቶ ኃይሉ ያነሱት፡፡ በዚህም አካባቢውን በተፈጥሮ መሸፈን እንዲሁም ምርታማነትን መጨመር ላይ እየተሰራ ነው ብለዋል፡፡ አቶ ኃይሉ አሁን ላይ ብዙዎች ትኩረት የሚሰጡት ለእምቦጭ ቢሆንም ከዚህ ባልተናነሰ ግን ደለልም የጣና ከፍተኛ ችግር መሆኑንም ተናግረዋል፡፡ በዚህም መሰረት የደብረ ታቦር ዩኒቨርሲቲ እስካሁን 41 ሺህ ችግኞችን የተከለ ሲሆን ይህም በሰባት ቦታዎች መከናወኑን ነው ተቋሙ ያስታወቀው፡፡
በዚህ ሂደትም ውጤት ለማምጣት በጣና ዙሪያ የሚገኙ ዩኒቨርሲቲዎች በተቀናጀ መልኩ ሥራዎችን እየሰሩ መሆኑ ተገልጿል፡፡ በዚህ ሂደትም በዩኒቨርሲቲው ጥረት 47 ሄክታር የሀይቁ አካል ከአምቦጭ መጽዳቱን አቶ ኃይሉ ገልጸዋል፡፡ ቀደም ሲል ጣና ሐይቅን ከእምቦጭና ከደለል አለመታደግ በሌሎች ፕሮጄክቶች ላይም አደጋ መሆኑን የገለጹት ዶክተር ዐቢይ ‘‘ጣናን ካልታደግን ሌሎች ፕሮጀክቶችም አደጋ ውስጥ ይወድቃሉ፤ የታላቁ የሕዳሴ ግድብ ውኃ ምንጭም ነውና’’ ሲሉም ትኩረት የተሰጠው ጉዳይ እንደሆነ መግለጻቸው ይታወሳል፡፡
የውሃ ስነ ምህዳር ተመራማሪውና የጣና ሐይቅና ሌሎች ውኃማ አካላት ጥበቃና ልማት ኤጀንሲ ዋና ሥራ አስኪያጅ ዶ/ር አያሌው ወንዴ ይህ አረም ቶሎ የማይጠፋ ከሆነ ወደ ህዳሴው ግድብ ሊጓጓዝ እንደሚችል ጠቁመዋል፡፡ አረሙ ወደ ግድቡ የግንባታ ሥፍራ ሳይደርስ እንደማይቀርም ባለፈው ሚያዚያ ወር ላይ ግምታቸውን ማስቀመጣቸው ይታወሳል፡፡