“የእምቦጭ አረም ሕዳሴ ግድብ ሳይደርስ አይቀርም”፡ የዶ/ር አያሌው ግምት
የጣና ሃይቅን 4ሺ ሄክታር ሸፍኖ የነበረው እምቦጭ አሁን ላይ 1ሺ ሄክታር መሸፈኑን ዶ/ር አያሌው ተናግረዋል
እምቦጭ የግድቡም ስጋት ቢሆንም “እንኳን የፌደራል መንግስት የክልሉ መንግስትም ኤጀንሲ ከማቋቋም የዘለለ ነገር” አለማድረጉን ዶ/ር አያሌው ገልጸዋል
እምቦጭ የግድቡም ስጋት ቢሆንም “እንኳን የፌደራል መንግስት የክልሉ መንግስትም ኤጀንሲ ከማቋቋም የዘለለ ነገር” አለማድረጉን ዶ/ር አያሌው ገልጸዋል
በኢትዮጵያ ትልቁ ሃይቅ፣ ጣና የባህር ዳር ከተማ ልዩ መለያና ድምቀት በመሆኑ ብዙዎች ለመዝናናት፣ለጥናትን ምርምር፣ ለኮንፈረንስና ለሌሎችም ምክንያቶች ወደሥፍራው ያቀናሉ፡፡
ጣና የዓለም የብዝሃ ህይወት ሀብት ሆኖ በተባበሩት መንግስታት የትምህርት፣ የሳይንስ እና የባህል ድርጅት (ዩኔስኮ) የተመዘገበው በ2007 ዓ.ም ነው፡፡ ይህ የዓባይ መነሻ ሀይቅ ታዲያ በመጤው የእንቦጭ አረም እየተጠቃ በመምጣቱ የአካባቢውን ነዋሪዎችና የቱሪዝም ባለሙያዎችን ስጋት ላይ ጥሏል፡፡
የዛሬ ዓመት ገደማ በምስራቃዊ የጣና ክፍል በፎገራ እና ደንብያ አቅጣጫ ጣና በአረም እየተወረረ ሁለት ኪሎ ሜትር አካባቢ ወደ መሀል ገብቶ እንደነበር የአካባቢው ነዋሪዎች ሲገልጹ ነበር፡፡ በዚህም “ጣና መሀሉ ሁሉ ዳር እየሆነ ነው” የሚል ፍራቻ ተከስቶ ከፍተኛ ስጋት ነበር፡፡ በዚህ የእቦጭ አረም ምክንያት በጐንደር ዙሪያ አካባቢ ጣናን ከቦታው በአይን እንኳን ለማየት አስቸጋሪ እንደነበርና አረሙ በጣና ስር ያሉ ፍጥረታትን በሙሉ በማውደም እና ውኃውን በማድረቅ ላይም መሆኑ ሲገለጽ ቆይቷል፡፡
አረሙ በሃይቁ ላይ መኖሩ የታወቀው መቼ ነው?
የውሃ ስነ ምህዳር ተመራማሪውና በአሁኑ ወቅት የጣና ሐይቅና ሌሎች ውኃማ አካላት ጥበቃና ልማት ኤጀንሲ ዋና ሥራ አስኪያጅ ዶ/ር አያሌው ወንዴ እንቦጭ ለመጀመሪያ ጊዜ በሃይቁ ላይ መኖሩ የተረጋገጠው ነሀሴ ወር 2003 ዓ.ም መሆኑን እና መስከረም 2004 ዓ.ም የውኃ ስነ ምህዳር ተመራማሪዎች የእንቦጭ አረም መከሰቱን ለክልሉ መንግስት ማስታወቃቸውን ተናረዋል፡፡
በ2004 ዓ.ም አራት ሺህ ሄክታር በሚሸፍነው የሀይቁ ክፍል ላይ የተገኘው እንቦጭ በ2005 ዓ.ም ከ95 እስከ 99 በመቶ መቆጣጠር ተችሎ እንደነበር ተገልጿል፡፡ ከ2006 እስከ 2007 ዓ.ም እንቦጭ ላይ ትኩረት በማጣቱ ከአራት ሺህ እስከ 10 ሺህ የነበረው ስርጭት ከ40 ሺህ እስከ 50 ሺህ ሄክታሩን ሽፍኖት እንደነበር የተገለጸ ሲሆን በ2004 ዓ.ም አንድ ቀበሌ ላይ የነበረው እንቦጭ አረምም በ2007 ዓ.ም 20 ቀበሌዎችን ተቆጣጥሮ 120 ኪሎ ሜትር የሀይቁን ዳርቻ ሸፍኖም ነበር፡፡
የጣና እንቦጭ ከሌላው ዓለም በምን ይለያል?
በቪክቶሪያ ሀይቅ እና በደቡብ አሜሪካ ባሉ ሀይቆች እንቦጭ ተከስቶ እንደነበር የገለጹት ዶ/ር አያሌው በሱዳን እና በግብጽም እንቦጭ በየወንዝ እና በየሀይቅ ዳርቻቻው ተከስቶ ነበር ብለዋል፡፡
ዶክተር አያሌው በዓለም ላይ የጣና እንቦጭን ያህል በአጭር ጊዜ፣ ሰፊ ቦታን የሸፈነ አረም በዓለም የለም ያሉት ተመራማሪና ሃላፊው በግብጽ እና በሱዳን የተከሠተው የሀይቁን መሀል የሚጐዳ አልነበረም:: የጣናው ግን የአካባቢውን ብዝሀ ህይወት ሙሉ በሙሉ አውድሞ የውሀውን ህልውና ሁሉ የሚያጠፋ ነው፡፡ ጣናን የብስ (ደረቅ መሬት)የማድረግ ጉልበት አለው፡፡ እንቦጭ ውሃውን ጨርሶ ይደርቃል፡፡
አርሶ አደሮቹ አረሙን ለማጥፋት ቁርጠኛ እንዲሆኑ ምን ቢደረግ ይሻላል?
በጣና ሃይቅ ላይ የተንሰራፋውን እምቦጭ ለማጥፋት ከፍተኛ ስራ እየሰሩ የሚገኙት አርሶ አደሮች መሆናቸው ይገለጻል፡፡ ይሁንና አረሙን ለማጥፋት ገንዘብ ስለሚከፈላቸው አረሙን ቶሎ ማጠናቀቅና አለማጠናቀቅ ከገንዘቡ ጋር ይያያዛል የሚሉ አስተያየቶች ይሰማሉ፡፡ ዋና ስራ አስኪያጁ ታዲያ አሁን ላይ አረሙን ለማጥፋት ለአርሶ አደሮች ተለክቶ እንደሚሰጥ አረጋግጠዋል፡፡ 200 ካሬ ሜትር እየተለካ እንደሚሰጥና ከዚህ በፊት በመለካት ያልተሠጠው አመቺ ስላልነበር ነው ብለዋል ዶ/ር አያሌው፡፡
አረሙ አሁን ምን ደረጃ ላይ ነው?
የጣና ሐይቅና ሌሎች ውኃማ አካላት ጥበቃና ልማት ኤጀንሲ ዋና ሥራ አስኪያጅ ዶ/ር አያሌው ወንዴ የእምቦጭ አረም የጣና ሃይቅን ወደ 4ሺ ሄክታር ይዞታ ሸፍኖት የነበረ ሲሆን አሁን ላይ ግን 1 ሺ ሄክታር የውኃ ክፍልን መሸፈኑን አስታውቀዋል፡፡አረሙን ሙሉ በሙሉ ለማጥፋት ታስቦ እንደነበር ያነሱት ዋና ሥራ አስኪያጁ አሁን ላይ ያለው የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ እንዳስተጓጎለው ተናግረዋል፡፡
አርሶ አደሮች አረሙን ለማጥፋት እየሰሩ ያለው ስራ ከሁሉም በላይ ውጤታማ መሆኑን ያነሱት ዶ/ር አያሌው ከህዳር ጀምሮ በ7 ወረዳዎች ላይ ከፍተኛ ስራ ለመስራ ታስቦ በአምስቱ ላይ ሲሳካ በሁለቱ አልተሳካም ብለዋል፡፡በሁለቱ የደንቢያ ወረዳዎች ፣በጣቁሳ፣ፎገራ፣ደራ፣ አረሙን የመልቀምና የማቃጠል ስራ ብቻ እንደሚቀርና ህብረተሰቡ የሚችለውን እያደረገ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
ይህ ስራ ግን በመንገድና በቁሳቁስ እጥረት ምክንያት በሊቦ ከምከም እና ጎንደር ዙሪያ ወረዳዎች አለመሰራቱን የገለጹት ዋና ሥራ አስኪያጁ መንግስት ማቅረብ የነበረበትን የመኪናና ሌሎች ግብዓቶችም አላቀረበም ብለዋል፡፡ አሁን ላይ ግን ቀደም ካለው ሁኔታ የባሰ ነገር አለመፈጠሩንም ገልጸዋል፡፡ ክረምቱንም በጀልባና በሰው ብዙ ስራ እንደሚሰራ የተገለጸ ሲሆን በትጋት ቢሰራ ተስፋ ሰጭ ነው ብለዋል፡፡
በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ለዚህ ስራ ድጋፍ እንዲያደርጉም ጠይቀዋል ዶ/ር አያሌው፡፡
ከዚህ በፊት የነበሩት ማሽኖች ጉዳይ ምን ላይ ደረሰ?
ከዚህ ቀደም ሀይቁን ለመታደግ የተገዙና በዩኒቨርሲቲዎች የተዘጋጁ ማሽኖች ካለው ችግር ጋር የመገናኘት ችግር እንዳለባቸው ያነሱት ሃላፊው ማሽን ሲመጣ ከሀይቁ ባህሪ ጋር መዛመድ አለበት ብለዋል፡፡ የተጠኑ አይደሉም፤ አረሙ የሚገኘው ከሁለት ሜትር በታች ባለው የሀይቁ ዳርቻ ላይ እንደሆነ የተገለጸ ሲሆን የዚህ ቸግር ምንጭ ቀድሞ ባለቤት ስላልነበረው መሆኑ ተገልጿል፡፡
ከዚህ ቀደም ሁሉም የራሱን አስተዋጽኦ ማበርከቱ የሚደገፍ መሆኑ የተነገረ ሲሆን ተናቦ መስራት ግን አስፈላጊ ነበር ብለዋል፡፡
በቱሪዝምና ባህል ላይ አተኮሮ የሚዘግበው ጋዜጠኛ ሄኖክ ስዩም የጣና ጉዳይ በእግጁ እንደሚያሳስበው ይገልጻል፡፡“ጣና ታሟል” የሚለው ጋዜጠኛው “ብዙ ሰው ስለ ግድቡ ሙሌትና ይናገራል”፤ በዚያው ልክ ግን የአባይ ወንዝ መነሻ የሆነው የጣና ሀይቅ ጉዳይ ሊያሳስበው ይገባል ብሏል፡፡
ያለ ጣና ሀይቅ ዓባይን ማሰብ እንደማይቻል ሄኖክ ይናገራል፡፡ ጣና ሀይቅን የወረረውንና በፍጥነት እየተስፋፋ ያለውን መጤ አረም ማጥፋት የግድ እንደሚል ጋዜጠኛ ሄኖክ ለአል ዐይን አማርኛ ተናግሯል፡፡
የፌዴራል መንግስት ስለ ጣና ምን ያለው አለ?
የጣና ሃይቅ ብሔራዊ ብቻ ሳይሆን ዓለም አቀፋዊ ሀብት መሆኑ የተረጋገጠ ጉዳ ሆኖ ሳለ ትኩረት ግን እየተሰጠው አለመሆኑን ብዙዎች ያነሳሉ፡፡ እንኳንም የፌዴራል መንግስት የክልሉ መንግስትም ኤጀንሲ ከማቋቋም የዘለለ ነገር እንዳላደረገም ተመራማሪውና ሃላፊው ዶ/ር አያሌው ያነሳሉ፡፡ ጉዳዩ የሚመለከተው የውኃ መስኖና ኢነርጅ ሚኒስቴር የሥራ ኃላፊን ለማነጋገር ተደጋጋሚ የስልክ ጥሪ ብናደርግም መልስ ልናገኝ አልቻልንም፡፡
በሀገሪቱ መዲና ሰው ሰራሽ መናፈሻ ቦታዎችን ለመስራት ጥረት እየተደረገ መሆኑን የሚያነሱት አስተያየት ሰጭዎች የጣና ጉዳይ ትኩረት እንዳልተሰጠው ያነሳሉ፡፡ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድና በሰኔ ወር አጋማሽ የተገደሉት የቀድሞው የአማራ ክልል ፕሬዚዳንት አምባቸው መኮንን (ዶ/ር) በጣና ላይ የተከሰተውን እምቦጭ በተመለከተ በስፍራው ግብኝት ማድረጋቸው ይታወሳል፡፡
ይሁንና የሚመለከታው የፌዴራል ተቋማት ስለሃይቁም ሆነ ስለገጠመው ችግር በይፋ የሰጡት አስተያየት አለመኖሩም ይነሳል፡፡
ሃይቁ የህዳሴው ግድብ መሰረት መሆኑን የሚያነሱት ዶ/ር አያሌው ይህ አረም ቶሎ የማይጠፋ ከሆነ ወደ ህዳሴው ግድብ ሊጓጓዝ እንደሚችል ጠቁመዋል፡፡ይህ አረሙ ወደ ግድቡ የግንባታ ሥፍራ ሳይደርስ እንደማይቀርም ግምታቸውን ተናግረዋል፡፡ እናም ዜጎች ስለግድቡ ያላቸው ብሔራዊ ስሜት ከውሃው መነሻ ጣና ሊጀምር ይገባል የሚል ሃሳብ ይነሳል፡፡