የአንድ ስታዲየም ስፋት ያለው የጠፈር አለት ከሰማይ ወደ መሬት እየተምዘገዘገ ነው ተባለ
ይህ አለት በከተማ ላይ ካረፈ የከፋ ጉዳት ሊያደርስ እንደሚል ተሰግቷል
የጠፈር አለቱ አሜሪካ በጃፓኗ ሂሮሽማ ላይ ከጣለችው ቦምብ 500 እጥፍ ሀይል አለውም ተብሏል
የአንድ ስታዲየም ስፋት ያለው የጠፈር አለት ከሰማይ ወደ መሬት እየተምዘገዘገ ነው ተባለ፡፡
የአሜሪካ ጠፈር ሳይንስ ምርምር ማዕከል ወይም ናሳ እንደገለጸው ከሆነ አሜሪካ በዓለም ጦርነት ወቅት በጃፓኗ ሂሮሽማ ላይ ከጣለችው ቦምብ በመቶዎች እጥፍ ሀይል ያለው የጠፈር አለት ወይም አስተሮይድ ወደ ምድር እየመጣ ነው ብሏል፡፡
የአንድ ስታዲየም ስፋት መጠን አለው የተባለው ይህ የጠፈር አለት በመጠኑ ባለፉት ስምንት ዓመታት ወደ ምድር ከመጡት ውስጥ ትልቁ እንደሆነ ተገልጿል፡፡
አፍሪካ፣ ፓስፊክ፣ እስያ እና ደቡብ አሜሪካ ይህ ጠፈር አለት ያርፍበታል ተብሎ ከሚጠበቁ ቦታዎች መካከል ዋነኞቹ ናቸው፡፡
ኤኤፍፒ የጠፈር ሳይንስ ባለሙያው ብሩስ ቤትስን ዋቢ አድርጎ እንደዘገበው ከሆነ የጠፈር አለቱ እንዲሰባበር እና ጉዳት ወደ ማያደርስ ቦታ ለማሳረፍ ጥረቶች በመደረግ ላይ ነው፡፡
ዓለም አቀፉ የጠፈር አለት ማስጠንቀቂያ ማዕከል በበኩሉ ወደ ምድር እየመጣ ያለውን የጠፈር አለት ወይም አስተሮይድ ጉዳት ለመቀነስ ዓለም አቀፍ ትብብር እንዲደረግ ጥሪ አቅርቧል፡፡
ናሳ እንደተነበየው ከሆነ ይህ የጠፈር ዓለት አሁን ባለበት ፍጥነት መሰረት ወደ ምድር በፈረንጆቹ 2032 ላይ ወደ መሬት ይደርሳል፡፡
እስካሁን ባለው የጠፈር አለት ታሪክ ከ66 ሚሊዮን ዓመታት በፊት የተከሰተው ከፍተኛ ውድመት እንዳደረሰ የተገለጸ ሲሆን 75 በመቶ በምድር ላይ የነበሩ ስነ ህይወቶችን አጥፍቷልም ተብሏል፡፡
ዘጠኝ ኪሎ ሜትር ርዝመት ነበረው የተባለው ይህ የጠፈር ዓለት ባረፈበት ስፍራ ዳይኖሰሮችን ጨምሮ በርካታ ዝርያዎችን እንዳጠፋም ይታመናል፡፡
በቅርቡ ተከስቷል የተባለው የጠፈር አለት በ1908 በሳይቤሪያ የረፈ ሲሆን እስከ 2 ኪሎሜትር ርቀት ውስጥ ያሉ ዛፎችን እንዳቃጠለ ተገልጿል፡፡
አሁን ላይ ወደ ምድር እየመጣ ነው የተባለው ይህ ግዙፍ ዓለት የከፋ ጉዳት እንዳያደርስ ካይነቲክ ኢመፓክተር የተሰኘ ቴክኖሎጂን በመጠቀም ጉዳት ወደማያደርስ መልኩ መቀየር እንደሚቻል ባለሙያዎች ይናገራሉ፡፡
ይሁንና ይህንን ቴክኖሎጂ ለመተግበር ከፍተኛ ወጪ የሚጠይቅ ሲሆን ብዙውን ጊዜ የበለጸጉ ሀገራት ወጪውን የሚሸፍኑት በአለቱ ሊጠቁ እንደሚችሉ ከተገነዘቡ ብቻ መሆኑ ጉዳዩን አሳሳቢ ያደርገዋል፡፡