መንግስት፤ ህወሓት “ምርኮኞች”ን ለቅቄያለሁ የሚለው አለም አቀፉን ማህበረሰብ ለማሳሳት ነው አለ
“በምርኮኛ ስም” ሰርጎ ገቦችን ለእኩይ አላማ ማደራጀቱን ደርሰንበታል ብሏል መንግስት
ኢትዮጵያ መንግስት “ምርኮኛ ናቸው ተብለው የተለቀቁት ታግተው የቆዩ የመከላከያ ሰራዊት ቤተሰብ አባላት ናቸው” ብሏል
የኢትዮጵያ መንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ዛሬ ባወጣው መግለጫ ህወሓት ምርኮኛ ወታደሮችን ለቋል የሚለው ሀሰት ነው ሲል አስተባብሏል፡፡
ሰሞኑን ህወሓት በሰሜን ኢትዮጵያ በተካሄደው ጦርነት ወቅት ማርኬያቸዋለሁ ያላቸውን በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ለቅቄያለሁ ማለቱን የተለያዩ ሚዲያዎች መዘገባቸው ይታወሳል፡፡
የኢትዮጵያ መንግስት ይህ የህወሃት ድርጊት አለምአቀፉን ማህበረሰብ ትኩረት ለመሳብ የተደረገ “ሀሰተኛ ፕሮፖገንዳ” ነው ብሏል፡፡
“መንግስት ጉዳዩን አስመልክቶ እያደረገ ባለው ማጣራት በሽብር ቡድኑ ምርኮኞች ናቸው ተብለው የተለቀቁት አብዛኞቹ ዜጎች የመከላከያ ሰራዊት ከትግራይ ክልል ለቆ በወጣበት ወቅት በሽብር ቡድኑ ታግተው የቀሩ የሰራዊቱ ቤተሰብ አባላት መሆናቸው ታውቋል።”
ከሰራዊት ቤተሰቦች በተጨማሪም ህወሃት በአፋር እና በአማራ ክልል በቆየባቸው ወቅት በግዳጅ ይዞ ኢሰብአዊ ድርጊት ሲፈጽምባቸው የነበሩትን ሰዎች እና “ከልዩ ልዩ የሃገሪቱ አካባቢዎች ለስራ ትግራይ ክልል ውስጥ ይኖሩ የነበሩ ሲቪል ነዋሪዎችን” ምርኮኛ ማስመሰሉን መንግስት ገልጿል፡፡
መንግስት ህወሓት ፖለቲካዊ ትርፍ ለማግኘት በማሰብ “የተለያዩ ጸጥታ ሃይሎችን መለዮ በማልበስ በምርኮኛ ስም አሰልፏቸዋል” ብላል፡፡
የህወሃት ድጋሚ ጦርነት ለመጀመር ያለውን ፍላጎት የሚሳይ ነው ያለው መግለጫው “በምርኮኛ ስም” ሰርጎ ገቦችን ለእኩይ አላማ ማደራጀቱን ደርሰንበታል ብሏል መንግስት፡፡
ሁለተኛ አመቱን በማገባደድ ላይ የሚገኘው እና ኢትዮጵያ በፊደራል መንግስት እና ትግራይን በሚያስተዳድረው ህወሓት መካከል የተጀመረው ጦርነት በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች እንዲገደሉ እና በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች እንዲፈናቀሉ ምክንያት ሆኗል፡፡
መከላከያ ሰራዊት ጦርነቱ ከተጀመረ 8 ወር በኋላ ከትግራይ ክልል መውጣቱን ተከትሎ ግጭቱ ወደ አማራ እና አፋር ክልሎች ተስፋፍቶ ሰብአዊ እና ቁሳዊ ውድመት መድረሱ ይታወሳል፡፡
የፌደራል መንግስት አስቸኳይ ጊዜ አዋጅ በማወጅና እና ክተት በማወጅ የትግራይ ኃይሎች ይዘውት ከነበሩት በርካታ የአማራ እና አፋር ክልል ቦታዎች ማስለቀቅ መቻሉን አስታውቆ ነበር፡፡ ነገርግን የህወሓት ኃይሎች ቦታዎቹን የለቀቁት መንግስት እንደሚለው ተሸንፈው ሳይሆን ለሰላም እድል ለመስጠት በማሰብ ነው ማለታቸውም እንዲሁ ይታወሳል፡፡
በመሀል ጦርነቱ ጋብ ያለ ቢመስልም የፌደራል መንግስት እና ሕወሓት በተለይ ከሰብአዊ እርዳታ አቅርቦት ጋር በተያያዘ እየተካሰሱ ይገኛሉ፡፡
በፌደራል መንግስት እና በህወሓት መካከል ያለው ግጭት በሰለም እንዲፈታ በአሜሪካ የሚደገፍና እና አፍሪካ ህብረት የሚመራ ንግግር እየተካሄደ ነው፤ ነገርግን በንግግሩ እስካሁን ይሄ ነው የሚባል ለውጥ አልመጣም፡፡
የፌደራል መንግስት ህወሓት የሀገረመንግስቱን ህልውና የሚፈታተን ተግባር ላይ ተሰማርቷል በሚል በአሸባሪነት መፈረጁ ይታወሳል፡፡