የኢትዮጵያ መንግስት አምርሮ የሚቃወመው ኤች አር6600 ረቂቅ ህግ ይዘት ምንድነው?
የኢትዮጵያ መንግስት የሰብአዊ እርዳታ እንዲደርስ ያስችላል ያለውን ተኩስ አቁም አውጇል
የአሜሪካ ኮንግረስ ኤችአር 6600 ረቂቅ ህግ በኢትዮጵያ ሰላምና መረጋጋት ለማምጣት እንደሚያስችል ይገልጻል
የአሜሪካ ኮንግረስ በግጭት ውስጥ ባለችው ኢትዮጵያ ሰላም፤መረጋጋትና የዲሞክራሲ ጥረቶች ይደግፋል ያለውን “የኢትዮጵያ መረጋጋት፣ሰላም እና ዲሞክራሲ አክት” (ኤች አር6600) የተሰኘ ረቂቅ ህግ አቅርቧል፡፡
የኢትዮጵያ መንግስት ይህ ረቂቅ ህግ በአሜሪካ ኮንግረስ እንዳይጸድቅ ተቃውሞ እያሰማ ይገኛል፡፡
ረቂቅ ህጉ በኢትዮጵያ ውስጥ ያለውን የእርስ በእርስ ጦርነት እና ሌሎች ግጭቶችን፤ ከፍተኛ የሰብአዊ መብት ጥሰቶችን፣ የጦር ወንጀሎችን፣በሰብአዊነት ላይ የተፈጸሙ ወንጀሎችን፤ የዘርማጥፋትን እና ሌሎች ግፎችን ለማስቆም ሁሉንም የዲፕሎማሲያዊ፣የልማት እና የግህ መሳሪያዎች ይጠቀማል ይላል፡፡
ከዚህ በተጨማሪም ህጉ በኢትዮጵያ ውስጥ የሰብአዊ መብት ጥሰት፤ የጦር ወንጀል፣ ዘር ማጥፋትን እና ሌሎች ግፎችን የፈጸሙ አካላት ተጠያቂ እንዲሆኑ ጥረት ያደርጋል፡፡
በረቂቅ ህጉ መሰረት፤ በኢትዮጵያ ከአመት በላይ ባስቆጠረው ግጭት ተሳታፊ የሆኑት የኢትዮጵያ እና የኤርትራ መንግስት እና የትግራይ ኃይሎችን ጨምሮ ሌሎች ተሳታፊዎች ማእቀብ እንደሚጣልባቸው ይገልጿል፡፡
የአሜሪካ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ከተለያዩ የአሜሪካ መስሪያ ቤቶች ጋር በመተባበር በኢትዮጵያ ከፍተኛ የሰብአዊ መብት ጥሰት የፈጸሙ የሚጠየቁበትን እና ግጭት ቆሞ እርቅ የሚወርድበት ስትራቴጂ እንደሚቀርጽ በረቂቅ ህጉ ተጠቅሷል፡፡
በረቂቅ ህጉ የተቀመጠውን ስትራቴጂ ለማሳካት፤ መፈጸም ያለባቸውን 10 ነጥቦች ዘርዝሯል፡፡
መፈጸም አለባቸው ተብሎው ከተዘረዘሩት ነጥቦች መካከል ከአፍሪካ ህብርት፣ከአውሮፓ ህብረት፤ከተመድ እና ከሌሎች ቀጣናዊ ተቋማት ጋር ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ማጠናከር፣ ያለገደብ ሰብአዊ እርዳታ ማድረስ፣ ቀውስ ሊያባብስ የሚችል የውጭ እርዳታ ማራቅና መለየት፣ የአሜሪካ ኢምባሲ ሰራተኞችን ደህንነት ማስጠበቅ፣የጥላቻ ንግግር መዋጋት፣ግጭቱን ለመፍታት ሁሉንም ብሄሮች ያካተተ ውይይት ማድረግ የሚሉት ዋና ዋናዎቹ ናቸው፡፡
ይህ ህግ ከጸደቀ ከ180 ቀናት ባልበለጠ ጊዜ ውስጥ እና ከ180 ቀናት በኋላ በወንጀል ተጠያቂ የማድረግ ሂደትን ሪፖርት ለሚመለከተው የኮንግረስ ኮሚቴ ያቀርባል፡፡
የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ግጭቱን በሰላም እንዲፈታ በሚደረጉ ጥረቶች ላይ እክል በሚፈጥር፤ የእርበእርስ ግጭቱ እና ሌሎች ግጭቶች እንዲስፋፉ ተባባሪ የሆነ፣የዘር ማጥፋትና የሰብአዊ መብት ጥሰት በፈጸመ፣ ሰብአዊ እርዳታ እንዳይደርስ ባደረገ እና በኢትዮጵያ ውስጥ በአፍሪካ ህበረት፣ በተመድ እና በሰብአዊ እርዳታ ሰጭ ሰራተኛ ላይ ጥቃት የፈጸመ አካል ላይ ማእቀብ እንዲጥሉ በረቂቅ ህጉ ስልጣን ተሰጥቷቸዋል፡፡
ከዚህ በተጨማሪም በግጭቱ ውስጥ በማወቅ የተሳተፋ፤ በግጭቱ ለተሳተፈ ማንኛውም አካል እርዳታ ያደረገ አካል ማእቀብ ይጣልበታል፡፡
በረቂቅ ህጉ ላይ ማእቀብ የሚጣልበት ሰው በአሜሪካ የሚኖር ከሆነ ንብረቱ እና የሚያደርገው ግብይት ሊታገድ ይችላል፡፡ ማእቀቡ ቪዛ የማገድ፣የመሰረዝ እና ወደ አሜሪካ እንዳይገባ ማድረግን ያካትታል፡፡
ሌላው በረቂቅ ህጉ የተካተተው ብዙዎችን ያሳተፋ ማእቀብ ወይም መልቲ ላተራል ማእቀብ ነው፡፡
በአሜሪካ የጦር መሳሪያ ዝርዝር ውስጥ የተካተቱ መሳሪያዎች ሁሉ ወደ ኢትዮጵያ እና ወደ ኤርትራ የሚደረግ ሽያጭ ፍቃድ እንደማይሰጥ ረቂቅ ህጉ ጠቅሷል፡፡
በረቂቅ ህጉ፣የኢትዮጵያ መንግስት ከእርበእርስ ግጭቱ ጋር የተገናኘ ወታደራዊ ዘመቻውን ካላቆመ፣ አካታች ውይይት ለማድረግ ካልተንቀሳቀሰ እና ሰብአዊ እርዳታ ያለገደብ የሚደርስበትን እድል ካልፈጠረ፣ ለኢትዮጵያ መንግስት የሚደረገው የጸጥታ ድጋፍ ይታገዳል፡፡
የአሜሪካ መንግስት በረቂቅ ህጉ፤ ለኢትዮጵያ የሚደረገውን አለም አቀፍ የገንዘብ ድጋፍ ውስን እንዲሆን ለማድረግ ትሰራለች፡፡ የአሜሪካው ገንዘብ ሚኒስትር በሁሉም አለምአቀፍ የፋይናንስ ተቋማት ያሉትን ተወካዮች መጠቀም፤ ተቋማቱ ለኢትዮጵያ እና ለኤርትራ የሚያደርጉትን ብድር፣ ብድር ማራዘም እና ማንኛውንም ቴክኒካዊ ድጋፍ ማድረግን እንዲቃወሙ ያደርጋል፡፡
በረቂቁ እንደተጠቀሰው ከሆነ አለም አቀፍ የፋይናንስ ተቋማት ማለት አይ አም ኤፍን፣ የአውሮፓ ባንክን፣የአፍሪካ ልማት ባንክን፣ባንክ ኦፍ ዴቨሎፕመንት ኤንድ ኮኦፐሬሽን ኢን ሚድል ኢስት ኤንድ ኖርዝ አፍሪካን ጨምሮ ከ10 በላይ አበዳሪ ተቋማትን ነው፡፡
በረቂቅ ህጉ መሰረት፣አሜሪካ ከሌሎች ለጋሽ ሀገራት ጋር በመሆን በኢትዮጵያ የሰብአዊ መብትን ለማሻሻል እና ሰላምን ለማምጣት የሚያስችል የብድር ስትራቴጅ ያዘጋጃል፡፡
ይህ ረቂቅ አዋጅ ከጸደቀ ከ180 ቀናት በኋላ የኢትዮጵያ እና የኤርትራ መንግስት ከፍተኛ ባለስልጣናት፣ ህወሓት፣ የታጠቁ ተቃዋሚዎች ወይም ተባባሪ ኃይሎች፣ በሰብአዊ መብት ጥሰት፣በጦር ወንጅል፣በዘርማጥፋት እና በሌሎች ኢትዮጵያ ውስጥ በተፈጸሙ ግፎች፣ ሰላማዊ ሰዎች ላይ እና በሲቪል በመሰረት ልማቶች ላይ በደረሰው ጥቃት ያላቸውን ተሳትፎ በመለየት የአሜሪካ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ለሚመለከተው ኮንግረስ ኮሚቴ ያቀርባል፡፡
ከዚህ በተጨማሪም ሚኒስቴሩ ከአሜሪካ የውጭ ገዳይ ሚኒስቴር ጋር በመተባበር ቱርክ፣ሩሲያ፣አረብ ኤምሬትስ፣ግብጽ፣ኢራን፣ሱዳን እና ቻይና በኢትዮጵያ በግጭት ውስጥ ላለ ማንኛውም አካል ያደረጉትን የገንዘብ እና የመሳሪያ ድጋፍ በመለየት ለኮንግሩ እንደሚያቀርብ ረቂቁ ላይ ተመልክቷል፡፡
ሪቂቅ ህጉ በግጭቱ ያላቸው ሚና ይለያል ያላቸው ከፍተኛ የመንግስት ባለስልጣናት ወይም ሌሎች አካላት ያስቀመጡባቸው የውጭ የገንዘብ ተቋማት እና ሆነብለው ጦር መሳሪያ ግዥ ወይም ዝውውር እንዲፈጸም ያመቻቹ የገንዘብ ተቋማት ተለይተው ይቀርባሉ፡፡
የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አምባሳደር ዲና ሙፍት በትናንትናው እለት በሰጡት መግለጫ ረቂቅ ህጉ “በአሜሪካ አስተዳደር በኩል በአሁኑ ሰአት የሚፈለግ አለመሆኑን” ተረድተናል ብለዋል፡፡
አስተዳደሩ ከኢትዮጵያ መንግስት ጋር ገንቢ በሆነ መልኩ የመስራት ፍላጎት ቢኖረውም ኮንግረሱ የህግ አውጭ አካል ስለሆነ አንዱ በአንዱ ላይ ሚያሳድረው ተጽእኖ ወሳኝ አይደለም ብለዋል አምባሳደር ዲና፡፡
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን ባለፈው ሳምንት “በመላው አሜሪካ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን የዳያስፖራ ወገኖች በአሜሪካ ምክር ቤቶች በኢትዮጵያ ላይ ለማሳለፍ የታቀዱት እጅግ አደገኛ ረቂቅ ህጎች እንዳይጸድቁ ከፍተኛ ዘመቻ እንዲያደርጉ” ጠይቀዋል፡፡
አንድ አመት ከሰባት ወር የሞላው በኢትዮጵያ ተቀሰቀሰው ግጭት፤ በሰላም እንዲፈታ አሜሪካ እና የአፍሪካ ህብረት ጥረቶች ጀምረዋል፡፡
በግጭቱ በትግራይ፣በአፋር እና በአማራ ክልሎች በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ህይወታቸውን ሲያጡ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች ደግሞ ከቀያቸው በመፈናቀል ኑሯቸው እንዲመሰቃቀል ሆኗል፡፡
የብልጽግና ፓርቲ በቅርቡ ባካሄደው ስብሰባ በኢትዮጵያ የተከሰተውን ግጭት ለመፍታት ማንኛውንም የሰላም አማራጭ እንደሚከተል አስታውቆ ነበር፡፡ የመንግስት ኮሙኒኬሽን ሚኒስቴር በትናንትናው እለት በሰጠው መግለጫ መንግስት የሰብአዊ እርዳታ በአግባቡ ወደ ትግራይ እንዲደርስ ለማስቻል የተኩስ አቁም ማወጁን ይፋ አድርጓል፡፡
የመንግስትን መግለጫ ተከትሎ ህወሓት በዛሬው እለት ባወጣው መግለጫ ሰብአዊ እርዳታ በአግባቡ ወደ ትግራይ የሚገባበት ሁኔታ ከተፈጠረ ተኩስ ለማቆም ቁርጠኛ መሆኑን አስታውቋል፡፡