በስህተት የደመወዙን 367 እጥፍ ክፍያ የተቀበለው የቀድሞ ሰራተኛም ገንዘቡን አልመልስም ብሏል
ለቀድሞ ሰራተኛው የአንድ ጊዜ ደመወዙን 367 እጥፍ የከፈለው የሀንጋሪው ኩባንያ።
ኩባንያው በአውሮፓ ሀንጋሪ ስሞጊ በተሰኘ ግዛት ውስጥ ያለ ድርጅት ሲሆን በስህተት ስራ ለለቀቀ የቀድሞ ሰራተኛው የአንድ ወር ደመወዙን 367 እጥፍ ከፍሏል ተብሏል።
ስሙ ያልተጠቀሰው ይህ ሰራተኛ በኩባንያው የሙከራ ጊዜውን እንዳጠናቀቀ ከስራ የተሰናበተ ሲሆን፤ በቆየባቸው ጊዜያት ውስጥ የሚገባው ክፍያ 238 ዩሮ ብቻ የነበረ ቢሆንም 92 ሺህ 549 ዩሮ በስህተት ተከፍሎተል ተብሏል።
ኩባንያው በስህተት ገንዘብ መክፈሉን ካወቀ በኋለ ሰራተኛው ገንዘቡን እንዲመልስ ሲጠይቅም ገንዘቡን የመመለስ ፍላጎት እንደሌለው ተናግሯል ተብሏል፡፡
ሰራተኛው ለኩባንያው በሰጠው መልስም እኔ የሀንጋሪ ባንክ ሂሳቤን ማንቀሳቀስ አልችልም ብሏል ሲል ኦዲቲ ሴንትራል ዘግቧል።
ኩባንያውም ጉዳዩን ወደ ህግ የወሰደው ሲሆን በተደረገው ምርመራም ግለሰቡ ገንዘቡን ወደ ሌላ አካውንት ማዘዋወሩን የሚያሳይ እንቅስቃሴ ማድረጉ ተደርሶበታል ተብሏል።
የሀገሪቱ ፖሊስም ገንዘቡ ያለበት የሂሳብ መዝገብ እንዳይንቀሳቀስ እና ወደ ድርጅቱ የባንክ ሂሳብ መዝገብ እንዲዞር በእንቅስቃሴ ላይ እንደሆነ በዘገባው ላይ ተጠቅሷል።
ከዚህ በተጨማሪም ያልሰራበትን ገንዘብ ተቀብሏል የተባለው የኩባንያው የቀድሞ ሰራተኛ ላይ ክስ ይመሰረትበታል የተባለ ሲሆን ጥፋተኛ ሆኖ ከተገኘ ከባድ ቅጣት እንደሚጠብቀው ተገልጿል።